በክልሉ ልማትን ለማስቀጠል የንግዱ ማህበረሰብ ግብር በወቅቱ በመክፈል የድርሻውን ሊወጣ ይገባል--- አቶ ለማ መገርሳ

102

አዳማ መጋቢት 14/2011 በክልሉ መንግስት የማስፈፀም አቅሙ አጠናክሮ ልማትን ለማስቀጠል በሚደረገው ጥረት የንግዱ ማህበረሰብ ግብር  በወቅቱ በመክፈል የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ  የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት  ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ አሳሰቡ፡፡

" ግዴታዬን ተወጥቼ መብቴን እጠይቃለሁ"በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀና በክልሉ ለአንድ ዓመት የሚቆይ ክልላዊ  የገቢ ግብርና ታክስ ንቅናቄ ዛሬ በአዳማ ይፋ ሆኗል፡፡

በዚህ ወቅት  የክልሉ መንግስት ፕሬዝደንት እንዳሉት መንግስት የሚያንቀሳቅሰው በቂ ሃብት ከሌለው የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ መመለስ አይቻልም።

" የለውጡ የጉዞ ፍጥነት የሚወሰነው በእጃችን የሚኖረው ሀብት ነው፤ የጀመርነውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሪፎርም ለማስቀጠል የገቢ ግብሩን አሟጠን ማስገባት አለብን "ብለዋል።

የክልሉ መንግስት የግብር መዋቅራዊ አደረጃጀቶችን እያስተካከለ መሆኑን አመልክተው በዓመቱ የክልሉ ገቢ እያደገ ቢመጣም ከሚሰበሰበው ውስጥ ከ46 በመቶ በላይ  የመንግስት ሰራተኞች ድርሻ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ይህም የሚያሳየው ከፍተኛውን ሀብት የሚያንቀሳቅሰው የንግዱ ማህበረሰብ ግብሩን በአግባቡ መክፈል እንዳለበትና ለዚህም መረባረብ እንደሚያስፈልግ ነው የተመለከተው።

ኦሮሚያ ከፍተኛ የሀገሪቱን ሀብት የሚያመነጭ ክልል እንደሆነ ያስረዱት አቶ ለማ የመንግስትን የማስፈጸም አቅም በማጠናከር ልማትን ለማስቀጠል  በክልሉ የሚገኘው የንግዱ ማህበረሰብ ከታክስ ስወራና ማጭበርበር በመራቅ ግብርን  በወቅቱ በመክፈል የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

"ኦሮሚያን መለወጥ ኢትዮጰያን መለወጥ ነው፤ ነጋዴዎች፣ የመንግስት ሰራተኞችና ባለሃብቶች የተጀመረውን ዘመቻ ከህዝቡና ከመንግስት ጎን ሆነው በበላይነት የመምራት ሃላፊነት አለባቸው" ብለዋል።

የኦሮሚያ ገቢዎች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ በበኩላቸው ንቅናቄው የተጀመረውን ክልላዊ ሪፎርም በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ለመደገፍ መሆኑን ተናግረዋል።

ገብር በተገቢው እንደማይሰበሰብ ገልጸው ለዚህም ትልቁ ማነቆ የሽያጭና የግዥ አሰራር ህጋዊነትን ያልተከተለ ፣ግልፅነት የጎደለውና የማጭበርበር ተግባር  መሆኑን አመልክተዋል፡፡

የተጀመረውን ሪፎርም ለማስቀጠልና የህዝቡን ጥያቄ በተገቢው መንገድ ለመመለስ የሚያግዝና ለአንድ ዓመት የሚቆይ የታክስ አሰባሰብ ንቅናቄ መጀመሩን አስታውቀዋል።

"በተጀመረው ንቅናቄ አርቲስቶች፣የኃይማኖት አባቶች ፣አባገዳዎችና በየደረጃው የሚገኙ ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ንቁ ተሳታፊ በመሆን ዓላማውን ማሳካት አለብን "ብለዋል።

ንቅናቄውን የሚያስፈፅሙ ከአትሌቶች፣ አርቲስቶችና የኃይማኖት አባቶች የተወጣጡ ታዋቂ ሰዎች የክልሉ መንግስት ፕሬዝደንት አቶ ለማ መገርሳ በግብር አምባሳደርነት ሾሟቸዋል።

በአዳማ ከተማ አባገዳ አዳራሽ በተካሄደው የንቅናቄው  ማስጀመሪያ ስነስርዓት ወቅት ከክልሉ ሁሉም ዞኖችና ወረዳዎች የተውጣጡ ከ1ሺህ 500 በላይ  የንግዱ ማህብረሰብ ፣ባለሃብቶችና ሌሎችም የህብረተሰብ  ክፍሎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም