የአጼ ቴዎድሮስ ጸጉር ብሔራዊ ሙዚየም ገባ

81

አዲስ አበባ መጋቢት 14/2011 በእንግሊዝ አገር የነበረው የአፄ ቴዎድሮስ ጸጉር በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም አቀባበል ተደረገለት።

ከ150 ዓመታት በላይ በብሪታኒያ ብሄራዊ ጦር ሙዚየም የነበረው የአፄ ቴዎድሮስን ጸጉር ኢትዮጵያ መጋቢት 11 ቀን 2011 ዓም መረከቧ ይታወሳል።

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሰው በእንግሊዝ ለንደን ተገኝተው ነበር የአጼ ቴዎድሮስ ጸጉርን የተረከቡት።

ዛሬ በብሔራዊ ሙዚየም በተደረገው የአቀባበል ስነ-ስርዓትም ሚኒስትሯ የእንግሊዝ መንግስት ይህን ታሪካዊ ውሳኔ በማሳለፍ ምላሽ በመስጠቱ  ምስጋና አቅርበዋል።

ለንደን የሚገኙ ሌሎች የኢትዮጵያ ቅርሶች ከእንግሊዞች ይልቅ ለኢትዮጵያዊያን በጣም የሚጠቅሙ የእድገትና ስልጣኔ ምንጮችና መሰረቶች ናቸውና እንዲመለሱ የምናደርገውን ጥረት አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።

መንግስት በተለያዩ አገራት የሚገኙ ቅርሶችን የማስመለስ ጥያቄውን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።

የአጼ ቴዎድሮስ ጸጉር ዛሬ ብሔራዊ ሙዚየም ሲገባ አርበኞች፣ አርቲስቶች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተው አቀባበል አድርገዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም