በኢትዮጵያ ዴሞክራሲና ስነ-ምግባር ተጣጥመው እየሄዱ ነውን?

49

አዲስ አበባ መጋቢት 14/2011 በኢትዮጵያ ዴሞክራሲና ስነ-ምግባር ተጣጥመው እየሄዱ ነውን?

"አንዳንድ ግለሰቦችና አካላት እንደ መንግስት መተወን ጀምረዋል። ይህ የሚያሳየው የመጣው ነፃነትና ዴሞክራሲ በዝቶ እንደሆን እንጂ አለማነሱን ነው።" ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በቅርቡ የተናገሩት ።

አንዳንዶች ደግሞ ይህ ዴሞክራሲና ነፃነት በስነ-ምግባር ካልታነፀ ውጤቱ ጥሩ ላይሆን ይችላል ብለው ይሞግታሉ።

የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት የለውጡን አንድ አመት አፈፃፀም አስመልክቶ ባዘጋጀው መድረክ ላይም የሚነሱት በርካታ አስተያየቶች "በአገሪቱ ዴሞክራሲና ስነ-ምግባር "ተጣጥመው እየሄዱ ነው? ወይስ አይደለም? የሚለውን በአንድም በሌላም መልኩ የሚጠይቁ ናቸው።

ይህንን በማስመልከት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሪፖርተር በመድረኩ ካገኛቸው ተሳታፊዎች ጋር በጉዳዩ ላይ ተወያይቷል።

የመጀመሪያ ጥያቄው እውን በኢትዮጵያ ዴሞክራሲና ስነ-ምግባር አብረው እየተተገበሩ ነውን? አሁን ባለው ሁኔታ የአገሪቱ ፖለቲከኞች፣ተሟጋቾችና ሌሎች አካላት ዴሞክራሲውን እንዴት እየተጠቀሙበት ነው? የሚለው ነው።

ተሳታፊዎቹ ኢትዮጵያ ለዴሞክራሲው ገና ተለማማጅ መሆኗን የሚስማሙ ሲሆን ይሁን እንጂ ዴሞክራሲና ስነ-ምግባር ከአሁኑ አብረው ካልሄዱ ውጤታቸው የምንጠብቀው ላይሆን ይችላል ይላሉ።

 ከፓርቲ አመራሮች መካከል አቶ አብርሃ ደስታ (የአረና ፓርቲ ሊቀ-መንበር) “ስልጣን እስካሁን ድረስ ህዝብን የምናገለግልበት መሳሪያ ሳይሆን ህዝብን የምንገዛበት፣ ሃብት የምንፈጥርበት፣ ክብር የምናገኝበት፣ ታሪክ የምንሰራበት ነው ስለዚህ በዛ ምክንያት አሁን እሽቅድድም ነው ያለው ወደ ስልጣን ለመውጣት ስለዚህ በዚህ ምክንያት ስነ-ምግባር አይኖርም ገና ወደ ዴሞክራሲ እየገባንም ስለሆነ ለዚህ ፈተና እየገጠመ ያለው" ብለዋል።

ምንም ነገር ስነ-ምግባር ይፈልጋል እንኳን ዴሞክራሲ ዴሞክራሲ ነው ብሎ የሰው ድንበር መጣስ አይቻልም። ስለዚህ ስነ-ምግባር በጣም ጠቃሚ ነገር ነው የሚሉት ደግሞ  ፖለቲከኛ ው አቶ ግርማ ሰይፉ ናቸው ፡፡

ህዝብን የሚያገለግል ትክክለኛ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት አሁን የመጣውን ነፃነትና ዴሞክራሲ ከስነ-ምግባር ጋር መተግበር እንደሚገባና ዴሞክራሲው በትክክለኛ ሃዲዱ ላይ ቆሞ ሁሉንም ዜጋ በእኩል አሳፍሮ መሄድ እንዲችል ሁሉም ያገባኛል ብሎ በንቃት ሊደግፈው ይገባል ይላሉ።

 ከውይይቱ ተሳታፊ ዶክተር ተስፋዬ ካሳ  ኢትዮጵያዊያን ዴሞክራሲን መለማመድ ስላቃተን በመግደል ወይም ቃላትን በማስ ሚዲያ ሰዎች እየተጠቀሙ አንድን ብሄር ከሌላው ጋር እንደሚያጣሉት ሳይሆን ገንቢ የሆኑ ሃሳቦችን እያፈለቅን በህብረተሰቡ ውስጥ እንዲሰርፅ እያደረግን ፈውስ መሆን እንችላለን፣ መድሃኒት መሆን እንችላለን ይችን አገር ወደ አንድ ደረጃ ልናደርሳት ይገባል ብለዋል ።

"ካልተሳተፍን ከፊል አምባገነን መንግስት ነው ልንመሰርት የምንችለው እንጂ ሙሉ ዴሞክራሲያዊ መንግስት ልንመሰርት አንችልም” ፖለቲከኛው አቶ ግርማ ሰይፉ ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም