በጎንደር ከተማ ደረሰኝ የማይቆርጡ ነጋዴዎች በግብር አሰባሰብ ላይ ጫና እያሳደሩ መሆኑ ተጠቆመ

58

ጎንደር  መጋቢት 14/2011 በጎንደር ከተማ የቫት ተመዝጋቢ ነጋዴዎች ለሚሸጡት እቃ በትክክል ደረሰኝ አለመቁረጣቸው በግብር አሰባሰብ ላይ ጫና ማሳደሩን የከተማው ገቢዎች መምሪያ አስታወቀ፡፡

ከቫት ተመዝጋቢዎች መካከል ዝቅተኛ አፈጻጸም ያላቸው 61 ነጋዴዎችን በመለየት እርምጃ መውሰድ መጀመሩንም መምሪያው አስታውቋል።

የመምሪያው የግብር አሰባሰብ፣ አወሳሰንና ክትትል የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ አየልኝ ዱቤ እንዳስታወቁት በከተማዋ ከ1 ሺህ 800 በላይ የቫት ተመዝጋቢ ነጋዴዎች አሉ፡፡

ከእነዚህ ነጋዴዎች በዓመቱ 121 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ እስካሁን 42 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ብቻ መሰብሰቡን ተናግረዋል፡፡

አንዳንድ ድርጅቶች በአግባቡ ደረሰኝ አለመቁረጥና ሌሎችም ለግል ጥቅማቸው ሲባል ለግዥ የሚሄዱ ደንበኞችን በደረሰኝ ከሚገዙበት ዋጋ ቅናሽ በማድረግ መሸጣቸው ለአፈጻጸሙ ዝቅተኛነት በምክንያትነት ጠቅሰዋል።

ይህን ችግር ለመፍታት የመምሪያው ባለሙያዎች በንግድ ድርጅቶች በመዘዋወር የክትትል ሥራ ሲያከናውኑ መቆየታቸውን አመልክተዋል፡፡

በዚህም ደረሰኝ በትክክል የሚቆርጡትን በማበረታታትና የማይቆርጡትን ደግሞ በመለየት የሚያቀርቡት የሽያጭ መዝገብ ተቀባይነት እንዳይኖረው መደረጉን አመልክተዋል፡፡

በዝቅተኛ አፈጻጸማቸው የተለዩ 61 ነጋዴዎች መኖራቸውን ገልጸው በግብር አሰባሰቡ ችግር ፈጥረው የተገኙ አራት ነጋዴዎች እያንዳንዳቸው በ50 ሺህ ብር እንዲቀጡ መደረጉንና፤ ይህ የማስተካከያ እርምጃም ተጠናከሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።

በተለይ በወርቅ ቤቶች፣ በህንፃ መሳሪያ መሸጫ ቤቶች፣ በኤሌክትሮኒክስ፣ በሸቀጣሸቀጥ፣ በፈርኒቸር እና በሥጋ ቤት የተሰማሩ ነጋዴዎች ላይ ችግሩ ጎልቶ እንደሚታይ ነው አቶ አየልኝ የገለጹት፡፡

እነዚህ ተቋማት የመመሪያው ባለሙያዎች በማይንቀሳቀሱበት ጊዜ ያለደረሰኝ ሽያጭ ያካሂዳሉ ተብለው ከተለዩት ውስጥ መሆናቸውንም አመልክተዋል፡፡

አቶ አየልኝ እንዳሉት በቀጣይ የግብር አሰባሰቡን ፍትሃዊ ለማድረግና ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ አሟጦ ለመሰብሰብ ህጋዊ እርምጃው ሕብረተሰቡን ባሳተፈ መንገድ ተጠናክሮ ለማስቀጠል እየተሰራ ነው፡፡

ሕብረተሰቡ ግብር መክፈል የዜግነት ግዴታና ለአካባቢ ልማት የሚደረግ የዜግነት ገዴታ መሆኑን ተረድቶ የሚያጭበረብሩ ነጋዴዎችን በማጋለጥ የበኩሉን እንዲወጣም አሳስበዋል፡፡

በህንጻ መሳሪያ ሽያጭ ሥራ የተሰማሩት አቶ አህመድ ጅብሪል በበኩላቸው እንዳሉት ደረሰኝ የማይቆርጡ ግለሰቦች በመንግስት ብቻ ሳይሆን በህጋዊ ነጋዴዎች ላይም ጫና እያሳደሩ ነው፡፡

ደንበኞቻቸው ያለደረሰኝ በቅናሽ ለመግዛት ሲሉ ወደ ህገ-ወጦች እንደሚሄዱ ጠቁመው የሚመለከተው አካል ተገቢውን ክትትል በማድረግ የማስተካከያ እርምት እንዲወስድ ጠይቀዋል፡፡

በኤሌክትሮኒክስ መደብር የተሰማሩት ወይዘሮ ፍርቱና አባይ በበኩላቸው እርሳቸው በደረኝ ቢሸጡም አንዳንድ ገዥ ደንበኞች ያለ ደረሰኝ እንዲሸጥላቸው የሚጠይቁበት ሁኔታ መኖሩን ገልፀዋል፡፡

"ፍትሃዊ የታክስ አስተዳደር በፌደራልም ሆነ በክልል ደረጃ ሊኖር ይገባል" ሲሉም ጠይቀዋል።

በጎንደር ከተማዋ ከ21 ሺህ በላይ ግብር ከፋዮች መኖራቸውን ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም