አዲስ ሕይወት ፈጥነን መመስረት እንድንችል ድጋፍ ሊደረግልን ይገባል...ወደቀያቸው የተመለሱ ተፈናቃዮች

52

ጎንደር መጋቢት 14/2011 ወደ አካባቢያችንብንመለስም ፈጥነን በማገገም አዲስ ሕይወት መመስረት እንድንችል ድጋፍ ሊደረግልን ይገባል ሲሉ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ወደ ጭልጋ ወረዳ የተመለሱ ተፈናቃዮች ተናገሩ፡፡

የጭልጋ ወረዳ አስተዳደር በበኩሉ እስካሁን ከ1 ሺህ በላይ አባወራዎች ወደቀያቸው ተመልሰው እራሳቸውን የማቋቋም ሥራ መጀመራቸውን አስታውቋል፡፡

በጭልጋ ወረዳ የላዛ ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር አለኸኝ ያለው እንደተናገሩት ላለፉት 3 ወራት በግጭት ምክንያት ተፈናቅለው በአይምባ ጊዜያዊ መጠለያ በእለት እርዳታ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡

አካባቢያቸው ወደ ቀደመ ሰላሙ በመመለሱ ወደቀያቸው ተመልሰው በቃጠሎ የወደመ ቤታቸውን ዳግም ለመስራት የቤት መስሪያ ቁሳቁስ እያሰባሰቡ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

" ወደ መኖሪያ ቀዬ ተመልሼ የሰላም አየር መተንፈሴ በራሱ ውስጣዊ ደስታ ተሰምቶኛል" ያሉት ደግሞ በወረዳው የላዛ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር ሞላ አለልኝ ናቸው፡፡

" ሰላም ካለ ሕይወት ወደ ነበረበት ይመለሳል፤ እኔም ይህን ተስፋ አድርጌ ቤተሰቤን በመጠለያ ትቼ  ቅድሚያ መኖሪያ ቤት ለመስራት ወደ መኖሪያ አካባቢዬ ተመልሺያለሁ " ብለዋል፡፡

"ተፈናቃዮች ከጉዳታችን ፈጥነን በማገገም አዲስ ሕይወት መምራት እንድንችል በመንግስት በኩል ተገቢ ድጋፍ ሊደረግልን ይገባል ሲሉም" ገልጸዋል።

አብዛኛው ተፈናቃይ አርሶ አደር በመሆኑ ክረምቱ ከመግባቱ በፊት የዘር የማዳበሪያና የእርሻ መሳሪያ እንዲቅርብላቸው የጠየቁት ደግሞ ከአይምባ መጠለያ ወደ መኖሪያ ቀያቸው የተመለሱት አርሶ አደር አግራው አለነ ናቸው፡፡

“በጎተራ ለዘር ያስቀመጥኩት እህልና የእርሻ መሳሪያ ጭምር ተዘርፎ ተወስዶብኝ ባዶ እጄን ቀርቻለሁ፤ ወደ እርሻ ስራዬ እንድገባ የመንግስት ድጋፍ ያስፈልገኛል” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

በወረዳው የአደዛ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ኑሪት ፈንታ በበኩላቸው "ከሦስት ወር የመጠለያ ቆይታ በኋላ ሰላማዊ ሁኔታ በመፈጠሩ ወደ ቀደመ መኖሪያ ቀበሌዬ ተመልሻለሁ" ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ምንም አቅም ስለሌላቸው መንግስትና የአካባቢው ሕብረተሰብ መኖሪያ ቤታቸውን ዳግም መስራት እንዲችሉ ድጋፍ ጠይቀዋል፡፡

የጭልጋ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አቡሃይ ጌትነት በበኩላቸው ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው በመመለስ ደረጃ እቅድ ወጥቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በወረዳው 7 ቀበሌዎች በነበረው የጸጥታ ችግር ከቀያቸው ተፈናቅለው በአይምባ ጊዚያዊ መጠለያ የነበሩ 1ሺህ አባዋራዎች በዚህ ሳምንት ወደ ወረዳው ተመልሰዋል፡፡

"በአሁኑ ወቅት የቤት መስሪያ እንጨት ቆረጣና የግንባታ ቦታ ሽንሸና ተጀምሯል" ያሉት አቶ አቡሃይ ስራውን የሚያስተባብሩ 300 የመንግስት ሠራተኞች መመደባቸውንም ተናግረዋል፡፡

አቶ አቡሃይ እንዳሉት በወረዳው 2 ሺህ 500 መኖሪያ ቤቶች በግጭቱ ወቅት የተቃጠሉ ሲሆን ቤት ለተቃጠለባቸው አባወራዎች ለእያንዳንዳቸው 50 የቤት ክዳን ቆርቆሮ ይሰጣል፡፡

"ተፈናቃዮቹ በዘላቂነት እስኪቋቋሙ ድረስ መንግስት ወርሃዊ ቀለብ ከማቅረብ ጀምሮ አርሶአደሮቹን ወደ ግብርና ሥራ ለማስገባት የሚያስችል ድጋፍ ይደረጋል" ብለዋል፡፡

ከማዕከላዊ ጎንደር ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በማዕከላዊ ጎንደር ተፈጥሮ በነበረው የጸጥታ ችግር 49 ሺህ 500 ተፈናቃዮች በጊዜያዊ መጠለያና ከዘመድ ጋር ተጠግተው ይገኛሉ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም