በመንግስትና በሕዝብ ገንዘብ ላይ ጉዳት ባደረሱ ሰዎች ላይ የክስ ማሻሻያ ተደረገ

107

አዲስ አበባ መጋቢት 14/2011 የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ በሚሆን ገንዘብ ላይ ጉዳት ባደረሱ ሰዎች ላይ የክስ ማሻሻያ አደረገ።

ተከሳሾቹ በበኩላቸው በአቃቤ ሕግ የቀረበባቸውን ክስ እንዳልፈፀሙ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል።

በእነ ሌተናል ኮሎኔል ተሰማ ግደይ የክስ መዝገብ ላይ በመንግስትና በሕዝብ ሃብት ላይ ጉዳት በአደረሱት 1ኛ ተከሳሽ ሌተናል ኮሎኔል ተሰማ ግደይ (ያልተያዙ)፣ በ2ኛ ተከሳሽ ሻለቃ መስፍን ስዩም እንዲሁም በ3ኛ ተከሳሽ አቶ ክፍላይ ንጉሴ ላይ ዐቃቤ ሕግ ያሻሻለውን ክስ ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል፡፡

ተሻሽሎ የቀረበው የዐቃቤ ሕግ ክስ እንደሚያመላክተው በ1ኛ እና በ2ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱት ተከሳሾች ለራሳቸው ጥቅም ለማግኘትና ለማስገኘት በማሰብ ከብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ግዥ መመሪያ ውጭ ያለምንም የገበያ ጥናትና ውድድር የማምረትም ሆነ የማቅረብ ፈቃድ ከሌለው 3ኛ ተከሳሽ ጋር ተመሳጥረዋል።

በመሆኑም ከ2004 እስከ 2006 ዓ.ም ሰባት የተለያዩ ሕጋዊ ያልሆኑ ውሎችን በመዋዋል 31 ሺህ የውሃ መርጫ (ሀይድራንድ) ምርቶች ግዥ እንዲፈፀም በማድረግ ያለ አግባብ የ10 ሚሊዮን 4 ሺህ 655 ብር ጉዳት አድርሰዋል፡፡

ተሻሽሎ የቀረበው ክስ ለተከሳሾች በጽሁፍ እንዲደርሳቸው ከተደረገ በኋላም በተሻሻለው ክስ ላይ አስተያየት የሌላቸው መሆኑን ገልጸዋል።

በዚሁ የክስ መዝገብ ላይ 2ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች 'ወንጀሉን አልፈፀምንም' ሲሉ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡

ዐቃቤ ህግ 1ኛ ተከሳሽ እስካሁን በፖሊስ ቁጥጥር ስር አለመዋላቸውንና ሌሎቹ ተከሳሾች ክሱን ክደው የተከራከሩ በመሆኑ ያሉኝ የሰነድ ማስረጃዎችና የምስክሮች ቃል እንዲሰማልኝ ሲል ፍርድ ቤቱን ጠይቋል፡፡

የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15ኛ የወንጀል ችሎትም የዓቃቤ ሕግን የማስረጃ ዝርዝርና የምስክሮችን ቃል ለመስማት ለግንቦት 15 እና 16 ቀን 2011 ዓ.ም ቀጠሮ ይዟል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም