የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና ነዋሪዎች ለተፈናቃዮች የ56 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረጉ

62

ዲላ መጋቢት14/2011 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና ነዋሪዎች ከምዕራብ ጉጂ ዞን ተፈናቅለው በጌዴኦ ዞን ለሚገኙ ዜጎች የ56 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረጉ።

ድጋፉን የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማን ጨምሮ የከተማዋ አመራር አካላትና የነዋሪ ተወካዮች በጌዴኦ ዞን ገደብ ወረዳ በመገኘት ትናንት አበርክተዋል፡፡

ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና ነዋሪዎች በአጠቃላይ ከተደረገው የ56 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ውስጥ 30 ሚሊዮኑ ከከተማው አስተዳደር በጥሬ ገንዘብ የተበረከተ መሆኑ ታውቋል።

ቀሪው ከነዋሪዎች የተደረገው የ26 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ድጋፍ ፍራሽ፣ መድኃኒት፣ ምግብ፣ አልባሳትና ሌሎች ቁሳቁሶችን ያካተተ ነው፡፡

ድጋፉን ለማበርከት ከአዲስ አበባ የተንቀሳቀሰውን ቡድን በመምራት በገደብ ወረዳ ገደብ እስታዲየም የሚገኙ ተፈናቃይ ዜጎችን የጎበኙት የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ናቸው።

ምክትል ከንቲባው ባዩት ነገር ማዘናቸውን ገልፀው ችግሩ ጊዜያዊ በመሆኑ ተፈናቃይ ወገኖች በሁኔታዎች ተስፋ መቁረጥ እንደሌለባቸው አመልክተዋል፡፡

ሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች ተቻችለውና ተከባብረው በጋራ እንዲኖሩ እንደመንግስት እየተከናወነ ያለውን ተግባር ለመደገፍ አስተዳደሩ ያላሰለሰ ጥረት እንደሚያደርግም አስረድተዋል ፡፡

"የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቀያቸው ተመልሰው በዘላቂነት እስኪቋቋሙ ድረስ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና ነዋሪዎች ከጎናቸው ይቆላሙ ሲሉም ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ቤልጅጌ በበኩላቸው በተፈናቀሉት ዜጎች መካከል መገኘታቸው ችግሩን ለማቃለል የሚደረገውን ጥረት ይበልጥ ትኩረት ሰጥቶ ለማገዝ የሚያነሳሳ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ለተፈናቃዮች የ30 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ለማድረግ በካቢኔ መወሰኑን ያስታወሱት አቶ ተስፋዬ ከከተማዋ ነዋሪዎችም የ26 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የአይነት ድጋፍ መደረጉን አብራርተዋል ፡፡

የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን ወክለው በስፍራው ከተገኙት መካከል አቶ ብርሀነ ግደይ የከተማዋ ነዋሪዎች ጉዳዩን በሚዲያ ከተከታተሉ በኋላ  ለወገናቸው የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ገልፀዋል፡፡

በአካል ተገኝተው ተፈናቃይ ዜጎች ያሉበት ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ መሆኑን ከተገነዘቡ በኋላ በግላቸው ተጨማሪ 300 ሺህ ብር ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል ፡፡

" ወደ አዲስ አበባ ስመለስም ሌሎች የከተማዋ ባለሀብቶችን በማስተባበር ተጨማሪ ድጋፍ ለማሰባሰብ ጥረት አደርጋለሁ " ብለዋል።

" ህዝቡ፣ መንግስትና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ተፈናቃዮች በዘላቂነት የሚቋቋሙበትን ሁኔታ ለማመቻቸት መስራት እንደሚጠበቅባቸው" የገለጹት ሌላው የከተማዋ ነዋሪ አቶ ሞሊቶ አባይነህ ናቸው።

የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገዙ አሰፋ በበኩላቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች፣ የከተማው አስተዳደር እንዲሁም በሀገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ወገኖቻቸውን ለመታደግ እያደረጉት ስላለው ሰብአዊ ድጋፍ አመስግነዋል ፡፡

አጋር ድርጅቶች እንዲሁም የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ባደረጉት ርብርብ ችግር ውስጥ ላሉ ተፈናቃይ ወገኖች ምላሽ መስጠት መቻሉን የተናገሩት ዋና አስተዳዳሪው በተለይ በገደብ ወረዳ ጎቲቲ ቀበሌ በአስከፊ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ህጻናትና እናቶች ችግር እየተቃለለ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡  

አቶ ገዙ አክለው እንዳሉት ህዝቡ ያሳየው ወገንተኝነት ተፈናቃይ ዜጎች አሁን ያሉበትን ሁኔታ ለመቀየር የሞራልና የግብዐት አቅም ይሆናል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም