በተለያዩ ምክንያቶች ግንባታቸው ተቋርጦ የነበሩ የውሃ ፕሮጀክቶች እንዲቀጥሉ ይደረጋል

87

አዲስ አበባ መጋቢት 14/2011 በወሰን ማስከበር ችግርና የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሳቢያ ግንባታቸው ተቋርጦ የነበረው የሳውዝ አያት ኖርዝ ፈንታ፣ የለገዳዲ ክፍል ሁለት ጥልቅ ጉድጓድ ውሃና ገርቢ ግድብ ግንባታቸው እንዲቀጥሉ እየተሰራ ነው።

የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን በአሁ ወቅት ከ550 ሺህ በላይ ደንበኞች ያሉት ሲሆን ከገፀ ምድርና ከርሰ ምድር የውሃ መገኛዎች በየዕለቱ 575 ሺህ ሜትር ኪዩብ ውሃ በማምረት በማድረስ ላይ ይገኛል፡፡

ከዚህ ውስጥም 46 ሺህ ሜትር ኪዩብ የሚሆነው የውሃ መጠን በያዝነው ዓመት ከኮዬ ፈጬ እና ኪስ ቦታዎች በተሰሩ የውሃ ፕሮጀክቶች የተገኘ ነው፡፡

አዲስ አበባ በፈጣን እድገት ውስጥ የምትገኝ በመሆኗ አሁን ያለው የቀን የውሃ ፍላጎት 930 ሺህ ሜትር ኪዩብ በላይ እንደሆነ ይገመታል፡፡

በመሆኑም አቅርቦትና ፍላጎቱን ለማጣጣም ታስቦ ከሁለት ዓመት በፊት ተጀምረው በወሰን ማስከበርና በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት ግንባታቸው ተቋርጦ የነበሩ ፕሮጀክቶች እንዲቀጥሉ ይደረጋል ተብሏል።

የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ባለፉት ዓመታት በሰራቸው በርካታ የውሃ ልማት ፕሮጀክቶች የውሃ ምርቱን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሳደገ መምጣቱንም ለኢዜአ በላከው መግለጫ አመልክቷል።

የዓለም የውሃ ቀን ዘንድሮ በዓለም ለ27ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ26ኛ ጊዜ "ንፁህ የመጠጥ ውሃ እና ሳኒቴሽን አገልግሎት ለሁሉ ተደራሽ ማድረግ" በሚል መሪ ሃሳብ ይከበራል፡፡

የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣንም በውሃ አቅርቦት፣ ተደራሽነት እና በዘመናዊ ፍሳሽ አወጋገድ እያከናወናቸው በሚገኙ ሥራዎች ዙሪያ ግንዛቤ በመስጠት እለቱን እንደሚያከብረው አስታውቋል።

እለቱ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ2030 ሁሉንም ህብረተሰብ የውሃ ተጠቃሚ ለማድረግ የተያዘውን አጀንዳ ታሳቢ በማድረግ ነው የሚከበረው።

ባለሥልጣኑ የከተማዋን የፍሳሽ አወጋገድ ሥርዓት ለማዘመን ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ባስገነባቸው የፍሳሽ መሠረተ ልማቶች የማጣራት ዓቅሙን በቀን 150 ሺህ ሜትር ኪዩብ አድርሷል፡፡

አሁን በቀን እያጣራ ያለው 85 ሺህ 500 ሜትር ኪዩብ ብቻ ነው፡፡

በዘመናዊ መንገድ ሰብስቦ ያጣራ ዘንድም ህብረተሰቡ የተዘረጉ የፍሳሽ መሠረተ ልማቶችን በአግባቡ እንዲጠቀም ጥሪውን አስተላልፏል፡፡

የዘንድሮው የውሃ ቀን የባለሥልጣኑ 500 የደንበኞች ፎረም አባላት፣ የከተማ አስተዳደሩ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በፓናል ውይይትና በፎቶ ኤግዚቪሽን ይከበራል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም