የክልሉን የውሃ ሃብት ከብክለት ጠብቆ ለትውልድ ለማቆየት ሁሉም ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል

71

ባህር ዳር/ወልዲያ መጋቢት 13/2011 በአማራ ክልል ያለውን የውሃ ሃብት ከሚደርስበት ብክለት ጠብቆ ለመጭው ትውልድ ለማቆየት ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍልና ተቋማት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተጠቆመ።

"ውሃና ሳኒቴሽን ለሁሉም ህብረተሰብ" በሚል መሪ ሀሳብ 27 ኛው ዓለም አቀፍ የውሃ ቀን በባህር ዳርና በወልዲያ ከተማ ዛሬ ተከብሯል።

በዓሉ በክልል ደረጃ በባህር ዳር ከተማ በፓናል ውይይት ሲከበር የክልሉ ውሃ፣ መስኖና ኢነርጅ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሞላ ፈጠነ እንደተናገሩት ያለውሃ ልማት፣ ዕድገትና ሕይወት ሊቀጥል አይችልም።

ከደንና ከተፈጥሮ ሃብት መመናመን ጋር ተያይዞ ታላላቅ የነበሩ ወንዞች፣ ኩሬዎችና ምንጮች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሲደርቁ ማየት የተለመደ ተግባር እየሆነ መምጣቱን ተናግረዋል።

"ለሕይወታችን በዋናነት አስፈላጊ ለሆነው ውሃ ተገቢ የሆነ ጥበቃ ባለመደረጉ እየደረሰ ያለውን ብክለት ለመከላከል ሁላችንም በባለቤትነት ልንጠብቀውና ልንከባከበው ይገባል" ብለዋል።

ውሃን የሚበክሉና ድርቅን የሚያባብሱ ነገሮች ወደውሃ እንዳይለቀቁ ተቀናጅቶ መስራት እንደሚገባ የተናገሩት ደግሞ የመወያያ ጽሑፍ ያቀረቡትና የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ይመር ሃብቴ ናቸው።

"የውሃ ሃብቱን በአግባቡ ጠብቀንና አልምተን መጠቀም ባለመቻላችን የገፅና የከርሰ ምድር የውሃ ሃብት እየቀነሰ እንዲመጣ ምክንያት ሆኗል" ብለዋል።

ይህም የደን መመናመን፣ የአካባቢው በረሃማነት እንዲስፋፋ እንዲሁም የወንዞች የፍሰት መጠን እንዲቀንስና በሂደትም ወንዞች እንዲደርቁ ማድረጉን አስረድተዋል።

ወደሐይቆች፣ ወንዞችና ሌሎች የውሃ አካላት የሚለቀቁ በካይ ነገሮችን ማስቆም ካልተቻለ በውሃ አካላት ላይ የሚደርሰው ተፅዕኖ ከዚህ የከፋ ሊሆን እንደሚችልም አቶ ይመር ስጋታቸውን ጠቁመዋል።

ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ የተጀመረውን የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራ አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ገልጸው፣ በተለይ በውሃ ሃብቱ ላይ የሚደርሰውን ብክለት ለመቀነስ የሁሉንም የተቀናጀ ጥረት እንደሚጠይቅ አመልክተዋል።

እንደ አቶ ይመር ገለጻ በክልሉ በቀን 650 ሺህ ሜትር ኩብ ውሃ ያስፈልጋል።

አሁን ባለው መረጃም በክልሉ ከተገነቡ 87 ሺህ የውሃ ተቋማት 15 ሺህ የሚሆኑት አገልግሎት መስጠት ያቆሙ ሲሆን ቀሪዎቹ ለሕብረተሰቡ በማገልግል ላይ ናቸው ።

ከፓናል ውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል የአማራ ውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ ተፈራ በበኩላቸው በክልሉ ለመጠጥ የሚውለው ውሃ 95 በመቶ የከርሰ ምድር ውሃ ነው።

በፊት እስከ 60 ሜትር ጥልቀት ላይ ይገኝ የነበረው ውሃ በአካባቢ መራቆት ምክንያት እየቀነሰ በመምጣቱ በአሁኑ ወቅት ውሃ ለማግኘት እስከ 600 ሜትር እርቀት መቆፈር የግድ እየሆነ መምጣቱን አስገንዝበዋል።

ችግሩ ከዚህ በበለጠ እየከፋ እንዳይሄድ የተራቆቱ አካባቢዎችን ወደነበሩበት ለመመለስ የተጀመረውን የተቀናጀ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ ማከናወን እንደሚገባም አሳስበዋል።

በፓናል ውይይት በተከበረው ዓለም አቀፍ የውሃ ቀን በዓል ላይ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

"በወልድያ ከተማ የውሃ ብክነቱ 26 በመቶ ደርሷል" ያሉት ደግሞ የሰሜን ወሎ ዞን ውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ መምሪያ ኃላፊ አቶ ሞገስ ቸርነት ናቸው፡፡

ለመጠጥ ውሃ ብክነትም በዋናነት ውሃና ፍሳሽ፣ ማዘጋጃ ቤት፣ ኢትዮ-ቴሌኮምና የኤሌክትሪክ አገልግሎት በጋራ መስራት አለመቻላቸው መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

"ችግሩን በጋራ ለመፍታት ጥረት ሲደረግ ቢቆይም አሁንም ችግሩ ሙሉ በሙሉ መፍታት አልተቻለም" ብለዋል።

አቶ ሞገስ እንዳሉት የውሃ ቀን የተከበረው በግንዛቤ እጥረት ለብክነት እየተጋለጠ ያለውን ውሃ በመቆጠብ ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚቻል በህብረተሰቡ ላይ ግንዛቤ ለመፍጠር ጭምር ነው።

በውይይቱ ከወልድያ ዩኒቨርሲቲና ከከተማው ማህበረሰብ ተወክለው የመጡ፣ የተቋማት ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ተገኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም