የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት ጉባኤ በመጪው እሁድ ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት ጉባኤ በመጪው እሁድ ይጀመራል
56
መቀሌ መጋቢት 13/2011 የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት አምስተኛ ዘመን 15ኛው መደበኛ ጉባኤ በመጪው እሁድ በመቀሌ ከተማ እንደሚጀመር ተገለጸ፡፡
የምክር ቤቱ ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ የምስራች ብርሃኑ ዛሬ እንደገለጹት ለሁለት ቀናት የሚካሄደው ጉባኤው የቢሮዎችን ያለፉት ስምንት ወራት የስራ አፈጻጸም ይገመግማል፡፡
ጉባኤው ከሚገምግማቸው መካከል የክልሉ ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ ለአርሶ አደሮች ለግብአት መግዣ የተሰጣቸው ብድር አመላለስና የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተከናወነ ያለውን አፈጻጸም ይገኝበታል፡፡
በክልሉ ውሀ ሀብት ቢሮ የሚያቀርበውን የመጠጥ ውሃና መስኖ ፕሮጀክት የአፈጻጸም ሪፖርት ላይ ምክር ቤቱ የሚወያይበት ሌለው ዘርፍ ነው፡፡
እንዲሁም የኮንስትራክሽን መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ከበጀት ዓመቱ መግቢያ ጀምሮ አስካሁን ያከናወናቸው የመንገድና የህንጻዎች ግንባታ አፈጻጸም ጉባኤው እንደሚመለከት ምክትል አፈ ጉባኤዋ አስታውቀዋል፡፡
ምክር ቤቱ በተጨማሪም በክልሉ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የተጠያቂነት ስርዓት ለማስፈን የወጣ እና የ2011 ዓ.ም. ተጨማሪ በጀት ረቂቅ አዋጆችን እንደሚያጸድቅ ይጠበቃል።