''በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም የተጀመረው መርሃ-ግብር ይጠናከራል''-የአማራ ክልል መንግሥት

72

ጎንደር  መጋቢት 13/2011 በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የተፈናቀሉ ወገኖችን  መልሶ ለማቋቋም የተጀመረው መርሃ-ግብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል  በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ መላኩ አለበል አስታወቁ፡፡

በአዲስ አበባ በተካሄደው የአማራ ልማት ማህበር(አልማ) የገቢ ማሰባሰቢያ ቴሌ ቶን የገንዘብ ድጋፍ ያደረጉ የአማራ ተወላጅ ባለሀብቶች  በአይምባና በአርባባ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ተፈናቃዮችን ጎብኝተዋል፡፡

አቶ መላኩ በዚህ ወቅት እንደተናገሩት የክልሉ መንግሥት በግጭቱ የተፈናቀሉ ወገኖች ከዕለት እርዳታ ጀምሮ በዘላቂነት የሚቋቁመበት መርሃ ግብር ነድፎ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡

''መንግሥት የአካባቢውን ሰላምና የሕግ የበላይነትን ለማስከበር ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው'' ብለዋል።

የክልሉ መንግሥት ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ የተጀመረውን ጥረት በማገዝ በኩልም ቤታቸው ለተቃጠለባቸው አባወራዎች 70ሺህ የቤት ክዳን ቆርቆሮ ዛሬ ወደ ጎንደር ከተማ መላኩን ተናግረዋል፡፡

ባለሀብቶቹ ጉበኝቱን የሚያደርጉት ተፈናቃዮች ያሉበትን ሁኔታ በማየት ድጋፋቸው የሚጠናከርበትን ሁኔታ ለመፍጠር እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

የባለሀብቶቹ ተወካይ አቶ ተካ አስፋው ''ባየነው ነገር ልባችን ተነክቷል፤ ከሞቀ ቤታቸው ተፈናቅለው ሴቶችና ህጻናት ጭምር ለተረጂነት መዳረጋቸው አሳስቦናል'' ብለዋል፡፡

ለወገን ደራሽ ወገን በመሆኑ ባለሀብቶች ድጋፋቸውን በማጠናከር ተፈናቃዮችን በማቋቋም የዜግነት ግዴታችን እንወጣለን ሲሉም ተናግረዋል፡፡

በአርባባ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ከሚገኙት ተፈናቃዮች መካከል አቶ ጋሻው ብርሃኑ እንዳሉት ''ረጅም ርቀት ተጉዛችሁ እኛን በአካል ለማየትና ችግራችንንም ለመካፈል ባለሀብቶች በመምጣታችሁ ከልብ ተደስተናል፡፡''

መንግሥት የጀመረውን ሰላም በማስፈን ወደ ቀያቸው በፍጥነት እንዲመለሱ የክልሉ አመራር ትኩረት እንዲሰጠው አሳስበዋል፡፡

በአማራና ቅማንት ሕዝቦች መካከል የተፈጠረው ግጭት የዜጎችን ሞት፣ የንብረት ውድመትና የዜጎች መፈናቀል አድርሷል ያሉት ደግሞ በአርባባ መጠለያ የሚገኙት አቶ መላኩ ውብነህ ናቸው፡፡

መንግሥት አቅሙ በፈቀደ ድጋፍ እያደረገላቸው መሆኑን የመሰከሩት አስተያየት ሰጪው፣ወደ መኖሪያ ቀያቸው በአፋጣኝ እንዲመለሱ ጥረት እንዲጠናከርላቸው ጠይቀዋል፡፡

ከዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በዞኑ በተቋቋሙ 13 ጊዜያዊ መጠለያዎችና ከዘመድ ጋር ተጠግተው የሚኖሩ ከ58ሺህ በላይ ተፈናቃዮች ይገኛሉ፡፡

ባለሀብቶቹ በጎንደር ከተማ በአባይ አክሲዮን ማህበር የተቋቋመውን የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ፋብሪካም ጎብኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም