በጥረት ኮርፖሬት የሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ አምስት ግለሰቦች በዋስ እንዲለቀቁ ተፈቀደ

66

ባህር ዳር መጋቢት 13/2011 በጥረት ኮርፖሬት የሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ አምስት ግለሰቦች በ100 እና በ150 ሺህ ብር ዋስ እንዲለቀቁ የባህር ዳርና አካባቢዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዛሬ ባስቻለው ችሎት ፈቀደ፡፡

የዋስትና መብት ለተፈቀደላቸው ሰዎች የውጭ ሃገራት ጉዞ እግዳ የተጣለ ሲሆን ፍርድ ቤቱ ክሱን ለማዳመጥ ለመጋቢት 26 ቀን 2011 ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

ችሎቱ ዛሬ የዋስትና ጉዳዩን ብይን ለመስጠት ባስቻለው ችሎት ከአቶ ታደሰ ካሳና ከአቶ ምትኩ በየነ ውጭ ያሉ አምስት ተከሳሾች በዋስ እንዲለቀቁ ወስኗል፡፡

በዚህም መሰረት በላፓልማ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ተጠርጥረው የተያዙት ወይዘሮ ቤተልሄም ብርሃኑ፣ ወይዘሮ እየሩሳሌም ብርሃኑና ወይዘሮ አይናለም ኃይለልኡል እያንዳንዳቸው በ100 ሺህ ብር ዋስ ተለቀው ጉዳያቸውን ከውጭ ሆነው እንዲከታተሉ ችሎቱ ፈቅዷል፡፡

ዋስትና የተፈቀደላቸው ተጠርጣሪዎች በበኩላቸው ከአንድ ቤተሰብ ለአንድ ጉዳይ 300 ሺህ ብር ዋስ ማስያዝያ ተገቢ እንዳልሆነና አቅማቸውም እንደማይፈቅድ ለፍርድ ቤቱ ቅሬታ አቅርበዋል፡፡

ችሎቱም " ቅሬታቸውን በጽሁፍ ሲያቀርቡ ውሳኔ ይሰጣል " ሲል አስታውቋል፡፡

በተጨማሪም በደሴ መደዶ ወይም ጃሪ ውሃ ፋብሪካ ጋር በሙስና የተጠረጠሩት አቶ ሁሴን አህመድ በተመሳሳይ በ100 ሺህ ብር ዋስ ወይም በበቂ የሰው ዋስ እንዲፈቱ ተፈቅዶላቸዋል፡፡

በባህር ዳር ሞተርስ ተጠርጥረው ክስ የተመሰረተባቸው አቶ ግርማቸው ዘውዱ በበኩላቸው 150 ሺህ ብር ዋስ አቅርበው በውጭ ሆነው እንዲከራከሩ ችሎቱ ፈቅዷል፡፡

የተጠርጣሪዎችን ህገ መንግስታዊ መብት ለማስከበር የተሰጠው የዋስትና ማስያዣ የሰዎችን ኢኮኖሚያዊ አቅም ያገናዘበ መሆኑን ችሎቱ አብራርቷል፡፡

ተጠርጣሪዎች የተከሰሱበት የሙስና ወንጀል በመሆኑና ከፍተኛ ሃብት በማባከን የተጠረጠሩ በመሆናቸው የውጭ ሃገራት ጉዞ እገዳ ተጥሎባቸዋል፡፡

ለተጠርጣሪዎቹ የዋስትና መብት የተፈቀደው የክልሉ የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን መርማሪ ቡድን ዋስትና ቢፈቀድላቸው የማይቃወም በመሆኑ ጭምር እንደሆነም በችሎቱ ተመላክቷል፡፡

ሁለተኛ ተከሳሽ አቶ ምትኩ በየነ ዋስትና ሊከለከሉ አይገባም ተብሎ በጠበቆቻቸው የቀረበውን አቤቱታ ፍርድ ቤቱ ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ የተከሳሾችን ክስ ለማዳመጥም ለመጋቢት 26 ቀን 2011 ዓ.ም ቀጠሮ የሰጠ ሲሆን በውጭ ሃገራት የሚገኙ ሁለት ተከሳሾችም ተይዘው እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡

አቶ ታደሰ ካሳ በበኩላቸው "የተሰጠው ቀጠሮ ረጅምና እኛን ሆን ብሎ ለመበደል እየተሰራ ነው" ሲሉ ቅሬታቸውን ያቀረቡ ሲሆን ችሎቱም የተገልጋይ ብዛት በመኖሩ ከተሰጠው ጊዜ በፊት ማየት እንደማይቻል በማስረዳት በተሰጠው የቀጠሮ ቀን እንዲቀርቡ ትዕዛዝ በመስጠት ችሎቱን አጠናቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም