ኢንስቲትዩቱ በአፋር ክልል የተከሰተውን የችኩንጉኒያ ወረርሽን ለመከላከል ጥረት እያደረገ መሆኑን ገለጸ

55

አዲስ አበባ መጋቢት 13/2011 የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በአፋር ክልል የተከሰተውን የችኩንጉኒያ ወረርሽኝ ለመከላከል ጥረት እያደረገ መሆኑን ገለጸ።

በሽታው በክልሉ በዞን አንድ አዳር ወረዳ ከየካቲት 29 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ መከሰቱ የታወቀ ሲሆን በሽታውን ለመከላከል በክልሉ ጤና  ቢሮ በኩል የተለያዩ ሥራዎች በመከናወን ላይ መሆኑን የቢሮው የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር (ፒኤችኢኤም) ሪፖርት ያሳያል፡፡

በሽታው ሪፖርት ከተደረገበት እለት ጀምሮ የክልሉ ፈጣን ምላሽ ሰጪ ቡድን፣ ከኢንስቲትዩቱ የሕብረተሰብ ጤና ባለሙያዎች፣ ኢንቲሞሎጅስቶች፣ የላባራቶሪ ባለሙያዎች እንዲሁም በክልል የሚንቀሳቀሱ አጋር ድርጅቶች በቦታው በመገኘት እየሰሩ ይገኛሉ፡፡

የተሰማራው ቡድን ባደረገው የመስክ አሰሳ አስር ታማሚዎች የተገኙ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ዘጠኙ የመገጣጠሚያና የጀርባ አጥንት ሕመም የራስ ምታትና ትኩሳት ስሜቶች እንዳሏቸው ኢንስቲትዩቱ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ ጠቅሷል፡፡

የመጀመሪያውን ታማሚ ጨምሮ ዘጠኙ ተመሳሳይ የሕመም ስሜት ካላቸው ሰዎች ጋር ግንኙነት እንደነበራቸው የገለጹ ሲሆን ስምንቱ የአልጋ አጎበር ተጠቃሚዎች እንደሆኑ ታውቋል፡፡

የችኩንጉኒያ በሽታ ወረርሽኝ ቆላማና ሞቃታማ በሆኑና ኤደስ ኤጂፕታይ የምትባል ትንኝ በምትራባበት አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ላይ የሚከሰትና  በትንኟ ንክሻ ምክንያት የሚተላለፍ የትኩሳት በሽታ ነው፡፡

በሽታው በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት በወረርሽኝ መልክ የሚከሰት ሲሆን በ2008 ዓ.ም. በኬንያ ድንበር አካባቢ ከነበረው ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ በኢትዮጵያም በሶማሌ ክልል ሊበን ዞን ዶሎ አዶ ወረዳ ተከስቶ የነበረና በተሰጠው ፈጣን ምላሽ መቆጣጠር መቻሉንም ተገልጿል፡፡

የበሽታው ምልክቶች ከፍተኛ ትኩሳት፣ ራስ ምታት፣ ድካም፣ የአይን መቅላት፣ ቁርጥማት፣ ማቅለሽለሽና ትውከት፣ የወገብ እጅና እግር ላይ የሚከሰት የቆዳ ሽፍታ፣ ከባድ የሆነ የእጅና እግር መገጣጠሚያ ሕመምና የመሳሰሉት ናቸው፡፡

በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ስለሚቻል ህብረተሰቡ ለሁሉም ባለድርሻ አካላትና ሌሎች ከሚመለከታቸው አስተባባሪዎች ጋር በመመካከር ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ ሲልም ኢንስቲትዪቱ አሳስቧል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም