ማእከሉ የመመረዝ አደጋ ለደረሰባቸው 450 ሰዎች ፈውስ ሰጥቷል

96

መጋቢት 13/2011 በቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የተቋቋመው የቶክሲኮሎጂ ምርምር ማዕከል ባለፉት ሶስት ዓመታት የመመረዝ አደጋ ለደረሰባቸው 450 ሰዎች ፈውስ መስጠቱን ገልጿል፡፡

ማእከሉ እነዚህን ፈውስ ይስጥ እንጂ የሚፈለገውን ያህል አገልግሎት ለመስጠት የማርከሻ መድሃኒትና የህክምና መሳሪያዎች  እጥረት  እንዳለበት ይጠቅሳል፡፡

የማእከሉ ኬዝ ቲም አስተባባሪ ዶክተር ጋዲሳ በዳዳ እንዳሉት ማእከሉ ከተመሰረተ ካለፉት ሶስት አመታት ወዲህ በፅኑ ለተመረዙ 450 ህሙማን ፈውስ ሰጥቷል፡፡

የአለም ጤና ድርጅት በየሃገሩ በሚያደርገው ግምገማ መሰረት ለኢትዮጵያ እንዲሁም ለጎረቤት ሃገራት አስጊ የሆኑ የጤና ችግሮችን አጥንቶ ከመመረዝ ጋር የተያያዙ ህመሞችን ለማከም ክፍተት በመታየቱ በ2009 ዓ.ም ማእከሉ እንዲመሰረት ምክንያት መሆኑም ነው የተገለጸው።  

ማእከሉ እንደ ኢትዮጵያ ብቻም ሳይሆን በምስራቅ አፍሪካ መመረዝን ለማከም ብቸኛ  የስፔሻሊቲ  ማእከል ሆኖ መቋቋሙንም ነው ዶክተር ጋዲሳ  ያወሱት ፡፡

ማንኛውም ነገር ከሚፈለገው መጠን በላይ ከተወሰደ ሊመርዝ እንደሚችል ያነሱት ዶክተር ጋዲሳ “ንፁህ ውሃ እንኳን  ከሚፈለገው በላይ ከተወሰደ ይመርዛል” ነው ያሉት ፡፡

ባለፉት ሶስት አመታት ለህክምና ወደ ማእከሉ ከመጡት 450 ታካሚዎች 90 ከመቶ ያህሉ ሆን ብለው መድሃኒቶችን ከመጠን በላይ በመውሰድ መመረዝ እንዳጋጠማቸው ገልፀው ከነዚህም ግማሽ ያህሉ የአእምሮ መታወክ ችግር እንዳለባቸው ጠቁመዋል ፡፡

የአእምሮ ችግር አጋጥሟቸው ህክምና እያደረጉ ያሉ ሰዎችም የታዘዘላቸውን መድሃኒት የመረበሽ ችግር ሲያጋጥማቸው “አንዴ የመውሰድ ሁኔታ አለ እዚህ ላይም የቤተሰብ ቅርብ ክትትል ያስፈልጋል” ብለዋል ፡፡

መድሃኒቶችን በመቆለፍ ለህፃናትም መጠንቀቅ ያስፈልጋል ያሉት ዶክተር ጋዲሳ ከውሃ ጋር ተመሳሳይነት ያላቸው ነጭ ጋዝና አሲዶችን በጥንቃቄ ማስቀመጥ እንደሚገባም ነው የገለፁት፡፡ 

በተለይ ክረምት አካባቢ በከሰል ጭስ  በተደጋጋሚ የመመረዝ ችግር እያጋጠመ በመሆኑ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

መመረዝ ሲከሰት ባለሙያን ማማከር እንደሚገባ የገለፁት ዶክተር ጋዲሳ በተለምዶ ውሃ መስጠትና  እንዲያስመልስ ማድረግ “ሊጠቅም እንደሚችል ሁሉ ሊጎዳ የሚችልበት አጋጣሚ አለ፤ በተለይ  ህፃናት መርዙ ወደ ሳንባቸው እንዲገባ ሊያደርግ ይችላል” ብለዋል ፡፡ 

ማእከሉ የሰው ሃይል፣ የዳያሊስስ ማሽን፣ አርቴፊሻል መተንፈሻዎች እና የሰውነት አሰራር የሚያሳዩ ማሽን እጥረቶችና ከነጭራሹም አለመኖር አጥጋቢ አገልግሎት እንዳይሰጥ ማድረጉም ተገልጿል ፡፡

በተለይ መመረዝን የሚያክሙና ህይወት አዳኝ የሆኑ አርቴፊሻል ቻርኮል፣ ናክና ፕራሲዶክሲሚ የሚባሉ ማርከሻ መድሃኒቶች  አለመኖሩን  የገለፁት ዶክተር ጋዲሳ  ማእከሉ የሌሎችን ሆስፒታሎች እገዛ በመጠቀም ጭምር ህይወት የማዳን ተግባሩን መቀጠሉን ነው የተናገሩት ፡፡

ወጣት አስቴር በለጠ መድሃኒት ከልክ ባለይ በመውሰዷ ምክንያት በማእከሉ ህክምና ስትከታተል ነው ያገኘናት፡፡

ወጣቷ እንዳለችው ባገኘችው የህክምና ክትትል የጤናዋ ሁኔታ እየተሻሻለ መጥቷል። ”የተረበሽኩበት ነገር ነበር” የምትለው ወጣቷ የተሰማኝ ብቸኝነት ለዚህ ውሳኔ ዳርጎኛል መፍትሄ ባይሆንም” ብላለች። ሃኪሞቹም የሚቻለውን እንክብካቤ እያደረጉላት መሆኑንም ነው የገለፀችው፡፡

የኢትዮጵያ የመድሃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ወይዘሮ አድና በሬ እንደገለፁት ማዕከሉ እንዲቀርብለት የሚፈልጋቸው መድሃኒቶች ኤጀንሲው በግዢ አቀርበዋለሁ ከሚላቸው 1ሺህ 373 ዝርዝሮች ውጪ መሆናቸውን ነው የጠቀሱት፡፡

ኤጀንሲው በዋናነት በሃገሪቱ ዋና ዋና የጤና ችግሮች ላይ ያተኮሩ መድሃኒቶችን እንደሚያቀርብ የጠቆሙት ዳይሬክተሯ ማእከሉ  የተጠቀሰውን መድሃኒቶች ከሌላ አቅራቢ ተቋም መግዛት እንደሚችልም ተናግረዋል፡፡

ማእከሉ መድሃኒቶቹን በግል አቅራቢዎችም ሆነ በጤና ሚኒስቴር በኩል ለማግኘት  እየሞከረ  ቢሆንም ሊሳካ አለመቻሉን ነው የገለፀው፡፡

የአለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም ማእከሉን በቅርቡ በጎበኙበት ወቅት ያለበትን የመድሃኒትና የህክምና መገልገያ መሳሪያ ችግር ለማቃለል ቃል መግባታቸውን ከማእከሉ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም