በሚቀጥሉት 10 ቀናት የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ የሆኑ አካባቢዎች ዝናብ ያገኛሉ

60

አዲስ አበባ መጋቢት 13/2011 በሚቀጥሉት 10 ቀናት የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ የሆኑ አካባቢዎች ላይ ዝናብ ሰጪ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች እንደሚጠናከርና ዝናብ እንደሚያገኙ የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ገለጸ።

ኤጀንሲው ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ባለከው መግለጫ እንዳስታወቀው በሰሜን ምስራቅ እና በደቡብ ምዕራብ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ላይ ዝናብ ሰጪ ሁኔታዎች እንደሚስፋፉ ገልጸዋል።

በዚህም በልግ አብቃይ በሆኑ አካባቢዎች ላይ ለእርሻ፣ ለአፈር እርጥበት፣ለቋሚ ተክሎች እና ለመጠጥ ውሃ አቅርቦት መጨመር እንዲሁም ለመኖ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ብለዋል።

ከኦሮሚያ ክልል ምስራቅና ምዕራብ ወለጋ፣ ጅማ፣ ኢሉአባቦራ፣ ምዕራብ ሸዋ፣ በአዲስ አበባ፣ ከአማራ ክልል ሰሜንና ደቡብ ወሎ፣ ዋግ ህምራ፣ ሰሜን ሸዋ፣ ምስራቅ ጎጀም፣ ምስራቅና ደቡብ ትግራይ፣ ከደቡብ ክልል ሀዲያ፣ ጉራጌ፣ ከፋ፣ ቤንቺ ማጂ፣ ወላይታ፣ ዳውሮ፣ ገሞ ጎፋ አንዳንድ ቦታዎች ላይ ዝናብ ይኖራቸዋል።

በተጨማሪም የምዕራብ አፋር ዞኖች፣ ደቡብ ጎንደር፣ ጋምቤላ፣ ምዕራብና ምስራቅ ሐረርጌ፣ አርሲ እና ባሌ ጥቂት ቦታዎች ዝናብ የሚኖራቸው ሲሆን የተቀሩት የአገሪቷ አካባቢዎች ደረቅ ሆነው ይሰነብታሉ።

በአካባቢው ያሉ አርብቶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮችም ውሃውን በመሰብሰብና በማቆር የውሃ ብክነትን መከላከል አለባቸው ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም