የአማራ ህዝብን ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር ግንኙነቱን ለማጠናከር መንግስት እንዲሰራ ተጠየቀ

90

ደብረማርቆስ መጋቢት 13/2011 የአማራ ህዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር ለዘመናት የዘለቀው ወንድማማች ግንኙነትን ለማጠናከር  መንግስት እንዲሰራ  የደብረማርቆስ ከተማ ነዋሪዎች ጠየቁ፡፡

ነዋሪዎቹ ይህንን የጠየቁት  በልማትና ወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ ከክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ጋር በቅርቡ በደብረማርቆስ ከተማ በተወያዩበት ወቅት በተለይ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ነው፡፡

የከተማው ነዋሪ አቶ ታምሩ ሰንደቁ እንዳሉት በሃገሪቱም ሆነ በክልሉ ከረጅም ጊዜ ትግል በኋላ ተስፋ ሰጭ ለውጥ ታይቷል፡፡

የተጀመረው ለውጥ ለፍሬ እንዲበቃና ዜጎች ያለስጋት እንዲኖሩ  ፍትህና የህግ የበላይነት  ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ ገልጸው በአንድነቷ ፀንታ የኖረችው ሃገር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ክፍተት መፈጠሩን አመልክተዋል፡፡

ይህም ዜጎችን በማፈናቀል ጉዳት መድረሱን ጠቅሰው የተጀመረው ለውጥ እንዳይደናቀፍ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ ለማጠናከር መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ ጠይቀዋል፡፡

"በተለይም ከትግራይ ህዝብ ጋር የሚስተዋሉ የግንኙነት መላለትን በማስተካካል የነበረውን የእህትና ወንድማማችነት እንዲሁም የመተሳሰብ እና የመቻቻል ባህላችን ማሳደግ ይገባል" ብለዋል፡፡

ከሌሎች ህዝቦች ጋርም  በአሉባልታ ወሬ የሚፈጠሩ ክፍተቶችን ለማስተካከል በሚነሱ ጉዳዮች ዙሪያ ተቀራርቦ በመነጋገር መፍታትም እንዲሁ፡፡

መንግስት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን አጠናክሮ ካልቀጠለ አንድ ኢትዮጵያን ለመገንባት አስቸጋሪ እንደሚያደርገው የተናገሩት ደግሞ አቶ አጥናፍ እያያው የተባሉ ነዋሪ ናቸው።

" በሁሉም ክልሎች የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት መጠናከር ይገባዋል" ብለዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከለውጥ በኋላ የተጠናከረ ግንኙነት ያላቸው ክልሎችን ማጥላላት እንደሚስተዋል አመልክተው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ ጠንካራ እንዲሆንና በጋራ ለአንድ አላማ ለመቆም አመራሩ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ ጠይቀዋል፡፡

ወይዘሮ እመነሽ ይግዛው በበኩላቸው ሀገር የሚለማው ፍቅር ፣ሰላምና መተሳሰብ ሲኖር በመሆኑ ይህንን በህዝብ ለህዝብ ግንኙነት መጠናከር እንደሚኖርበት አመልክተዋል።

የአንደኛው ክልል ከሌላው ክልል መልካም ግንኙነት እንዳይኖረው በማህበራዊ ድህረ ገጾች የሚለቀቁ ወሬዎችንም ሙሉ በሙሉ ማመን ተገቢ እንዳልሆነም ጠቁመዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር አምባቸው መኮንን በበኩላቸው " በህዝቡ  የፀና ትግል የመጣው ለውጥ በማንኛውም መንገድ አንድ ስንዝር እንኳ ወደ ዋላ አይልም" ብለዋል፡፡

የአማራን ህዝብ ከሌላው ጋር ለይቶ መምራትና ማስተዳደር እንደማይቻል ገልጸው " ከሌላው ህዝብ ጋር እኩል እንዲለማና እንዲያድግ ነው እየተሰራ ያለው "ብለዋል፡፡

" አልፎ አልፎ ፀብ አጫሪነት ይስተዋላል " ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ ይህን የአመራር ጥበብን ተጠቅሞ በኃላፊነት መንገድ መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

ፍቅርን፣ ሰላምን፣ አንድነትን፣ መተሳሰብን፣ በጋራ መልማትና መበልፀግን እውን በማድረግ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ለማጎልበት ጠንክረው እንደሚሰሩም አስታውቀዋል፡፡

የአዴፓ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዮሐንስ  ቧያለው በበኩላቸው ደርጅታቸው ከሁሉም ክልል ህዝቦች ጋር መልካም ግንኙነት እንዲኖረው ጽኑ አቋማ ይዞ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

በምንም ይሁን በምን የማይለያይን ማህበረሰብ ለመነጣጠል የሚደረጉ ክፍተቶችን በመነጋገር ለማስተካከል በከፍተኛ ኃላፊነት መንፈስ እየተሰራ እንደሆነም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም