በዘላቂነት ለመቋቋም መንግስት ድጋፍ እንዲያደርግላቸው በመቀሌ የተጠለሉ ተፈናቃዮች ጠየቁ

40

መቀሌ መጋቢት 13/2011 በዘላቂነት መቋቋም እንዲችሉ መንግስት ትኩረት ሰጥቷቸው ድጋፍ እንዲያደርግላቸው  በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በነበረው የጸጥታ ችግር  ተፈናቅለው በመቀሌ ከተማ የተጠለሉ  ዜጎች ጠየቁ፡፡

በከተማው ጊዜያዊ መጠለያ ከሚገኙት መካከል  አቶ መኮንን ሐዱሽ ለኢዜአ እንደገለጹት ቀደም ሲል ይተዳደሩበት የነበረውን የመጠጥና ምግብ  ንግድ ቤት ከአንድ ዓመት በፊት ተፈጥሮ በነበረው ችግር ወድሞባቸዋል።

አምስት ልጆቻቸውን ጨምሮ በነፍስ ወከፍ በየወሩ በመንግስት በሚቀርብላቸው 15 ኪሎ ስንዴና ግማሽ ሊትር ዘይት ህይወታቸውን እየመሩ መሆኑን ተናግረዋል።

ከጠባቂነት ተላቀው ራሳቸውና ልጆቻቸው ሰርተው ለማስተዳደር መንግስት የገንዘብና  የመስሪያ ቦታ  ድጋፍ እንዲያደረግላቸው ጠይቀዋል፡፡

ወጣት ሳምራዊት ዘርአይ በበኩሏ የነበራትን የንግድ ድርጅት  ከነሙሉ እቃው በወቅቱ ማጣቷን ገልጻለች፡፡

በመንግስት እየቀረበ ያለው ድጋፍ በቂ ባለመሆኑ ቤት ለቤት በመዞር በልብስ ማጠብ ስራ  ኑሮዋን ለመግፋት መገደዷን ተናግራለች፡፡

"መንግስት የሁሉንም ችግር በአንዴ ለመፍታት ባይችልም የከፋ ችግር ውስጥ የወደቅን ተፈናቃዮችን  በማጥናትና በመለየት  ቅድሚያ ትኩረት ሊሰጠን ይገባል "ብላለች፡፡

ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማቋቋም መንግስት ቀደም ብሎ ቃል የገባው ባለመፈጸሙ ትኩረት እንደሰጣቸው የጠየቁት ደግሞ ሌላው ተፈናቃይ አቶ ተስፋማሪያን ሃድጉ ናቸው፡፡

በመቀሌ ከተማ በጉልበት ስራ የሚተዳደሩት አቶ ገብረ ህይወት ፋንታሁን ካላቸው ገቢ ቀንሰው 400 ብር ለተፋናቃዮች ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

ገቢያቸው አነስተኛ ቢሆንም ካላቸው ውስጥ ማካፈላቸው ተፈናቃዩቹን ለማበረታታት ያግዛል ብለው እንደሚያምኑ አመልክተዋል፡፡

የክልሉ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ንግስቲ ወልደ ሩፋኤል በበኩላቸው  በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በነበረው የጸጥታ ችግር  ተፈናቅለው ወደ ክልሉ የገቡ ዜጎች ቁጥር ከ84 ሺህ በላይ መድረሱን ገልጸዋል።

ከተፈናቃዮቹ ውስጥ ከስምንት ሺህ በላይ ህጻናት ይገኙበታል።

ለህጻናቱ መንግስት ከአልሚ ምግብ በተጨማሪ ትምህርታቸውን በነጻ እንዲከታተሉ ድጋፍ ማድረጉን አስረድተዋል።

ተፈናቃዮቹ በዘላቂነት ለማቋቋም ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚያስፈለግ ያመለከቱት ወይዘሮ ንግስቲ የክልሉ መንግስት ገንዘቡን ከተለያዩ ድጋፍ ሰጪ ግለሰቦችና ተቋማት ለማስባሰብ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እስካሁን በተደረገው ጥረት 80 ሚሊዮን ብር ማሰባሰብ መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡

ገቢ የማሰባሰብ ስራውን በሀገር ውስጥና በውጭ በሚገኙ የክልሉ ተወላጆችና ደጋፊዎች ተሳትፎ ለማጠናከር የሚደረገው ጥረት መቀጠሉንም አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም