በኢትዮጵያ የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠል ጠንካራ ተቋማት መገንባት ያስፈልጋል - ምሁራን

122

አዲስ አበባ መጋቢት 13/2011 በኢትዮጵያ የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠል ጠንካራ ተቋማት መገንባት ያስፈልጋል ሲሉ ምሁራን ገለጹ።

በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት "አዲስ ወግ" በሚል ርዕስ የተዘጋጀው የሁለት ቀናት የውይይት መድረክ ዛሬ ተጀምሯል።

"የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ጉዞ ታሪካዊ ዳራና ወቅታዊ ተግዳሮት" በሚል መሪ ሐሳብ ላይ የታሪክ መምህርና ተመራማሪ ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው፣ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ተመራማሪ ዶክተር ዲማ ነገዎ፣ የፖለቲካ ሳይንስ ተመራማሪና መምህር ዶክተር ሰሚር ዩሱፍ እንዲሁም የፖለቲካ ፍልስፍና መምህርና አስተማሪ ኢክራም መሐሙድ በመድረኩ የውይይት መነሻ ሀሳብ አቅርበዋል።

ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው ለውጡ ከውስጥ የመጣ በመሆኑ በቀጣይ ጠንካራ ተቋማት መገንባት እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ በዚህ ረገድም የሲቪክ ተቋማት ወሳኝ ሚና ያላቸው በመሆኑ ሊጠናከሩ ይገባል ብለዋል።

የመንግስት ተቋማት ያላቸው የስራ ባህል ደካማ ከመሆኑም በላይ በሰው ሃይል የተጠናከሩም እንዳልሆኑ እንዲሁም አሁን ያለውን ለውጥ አስተካክለው ለመምራትና ለማስቀጠል የሚያስችል ብቃት የሌላቸው በመሆኑም ለለውጡ እንቅፋትና ተግዳሮት ሊሆኑ እንደሚችሉም አስረድተዋል።

ከተያዘው የለውጥ ሂደት ጋር በተያያዘም በኢትዮጵያ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች "ቆሞ ቀርነት" እንደሚታይባቸውም ጠቅሰዋል።

ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ በበኩሉ ለውጡን ለመሸከም የሚያስችል ቁመና ላይ መሆኑን ራሱን በመፈተሽ ማየት እንደሚገባው አመልክተዋል።

ለውጡ ከተጀመረበት መጋቢት 2010 ዓ.ም እስከ ነሐሴ 2010 ዓ.ም ድረስ ብቻ እንደዘለቀና ከዚያ በኋላ ግን ወደ ብሔር ፖለቲካነት መለወጡን ነው ያስረዱት ረዳት ፕሮፌሰር አበባው።

የፖለቲካ ኢኮኖሚ ተመራማሪ ዶክተር ዲማ ነገዎ በበኩላቸው በኢትዮጵያ የመጣው ለውጥ ከውጭ አገር የመጣ ሳይሆን በህዝብ ግፊት ከውስጥ የመነጨ እንደሆነ ገልጸዋል።

ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ እንደተካሄዱት የመንግስት ለውጦች በወታደራዊ ሃይል ያልታገዘ መሆኑንና የፖለቲካ መሸናነፍ የታየበት እንዳልሆነም አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅት ያለው ለውጥ ካለፉት 50 ዓመታት ጀምሮ የነበሩ የዴሞክራሲ፣ የመብት፣ የብሔር ብሔረሰቦችና የቋንቋ ጥያቄዎች ሲንከባለሉ የመጡበት ነውም ብለዋል።

የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠል ነጻና ገለልተኛ አገራዊና ህዝባዊ ተቋማትን መገንባት እንደሚያስፈልግና በፓርቲና በመንግስት መካከል የሚታየውን መደበላለቅ ድንበር ማበጀት እንደሚገባም አስረድተዋል።

በፕሮግራምና በዓላማ የተደራጁና ሰፊ ህዝባዊ መሰረት ያላቸው ፖለቲካ ፓርቲዎችን ማቋቋም እንደሚገባም አስረድተዋል ዶክተር ዲማ።

በህዝቦች ዘንድ ያልተመለሱ ጥያቄዎች፣ የተጠያቂነት ስርዓት አለመኖር እና የኢኮኖሚና የጸጥታ ጉዳዮች አሁንም ለውጡን የሚፈታተኑ ተግዳሮቶች እንደሆኑ ጠቁመዋል።

የፖለቲካ ሳይንስ ተመራማሪና መምህር ዶክተር ሰሚር ዩሱፍ እንዳሉት መንግስትን የሚገዳደር ሃይል እንዲፈጠር በማድረግ የፖለቲካ ምህዳሩን እንዲሰፋ ማድረግ ይገባል።

በመንግስት ላይ ጫና በማድረግ የሚገዳደረው ሃይል ከመንግስት ቁጥጥር ውጪ ያሉትን ተቋማት ህልውና የሚያጨልም መሆን እንደሌለበትም አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅት ያለው ለውጥ  ህዝባዊ ሳይሆን መንግስት መራሽ ለውጥ በመሆኑ የሲቪክ ማህበራት ሚና የቀጨጨ እንዲሆን ያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።

ተገዳዳሪ ሃይሎች የወል የሆነውን የዴሞክራሲ ስርዓት ከመገንባት ይልቅ የግል ጥቅማቸውን በአቋራጭ የማስጠበቅ ሩጫ ላይ እንደሚገኙም ተናግረዋል።

በአሁን ወቅት የሚታየው የብሔር ግጭትም ከዚህ በፊት የነበረው የአምባገናናዊ ስርዓት ውርስ እንደሆነም ዶክተር ሰሚር አብራርተዋል።

"ዴሞክራሲ ከመንግስት የሚሰጥ ገጸ በረከት አይደለም" ያሉት የፖለቲካ ሳይንስ ተመራማሪና መምህር ዶክተር ሰሚር፤ በፓርቲና በመንግስት መካከል ያለው መጣረስ መስተካከል እንደሚገባውም አመልክተዋል።

በኢትዮጵያ ያለውን የኢኮኖሚ ቀውስ፣ ኢ-ፍትሐዊ የሆነ የሀብት ክፍፍልና መካከለኛ ገቢ ያለው የህብረተሰብ ክፍል መቀጨጭን መንግስት ጣልቃ በመግባት ሊያስተካክለው እንደሚገባም አስረድተዋል።

የፖለቲካ ፍልስፍና መምህርና አስተማሪ ኢክራም መሐሙድ በበኩላቸው የዴሞክራሲን ጽንሰ ሐሳብ ከአገራዊ ነባራዊ ሁኔታ ጋር አገናዝቦ መመርመር ያስፈልጋል ብለዋል።

ዴሞክራሲ ያለ ስነ-ምግባር ብቻውን የሚሄድ ባለመሆኑም በስነ-ምግባር የታነጸ ዴሞክራሲ መገንባት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።

ምሁራኖቹ ባነሱት ሀሳብ ላይ ከተሳታፊዎች ጥያቄዎች ተነስተው ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።

የውይይት መድረኩ ከሰዓት ሲቀጥል የውጭ ጉዳይ ፖሊስና የአፍሪካ ተሳትፎን በተመለከተ ዘርፉን በተመለከቱ በአራት ባለሙያዎች የውይይት ሀሳብ እንደሚቀርብም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም