ተፈናቅለው በምዕራብ ወለጋ ዞን ለተጠለሉ ወገኖች ድጋፍ የሚውል የቶምቦላ ሎተሪ ሽያጭ እየተካሄደ ነው

60
ጊምቢ ግንቦት 23/2010 በኦሮሚያና በሶማሌ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ተከስቶ በነበረው ግጭት ተፈናቅለው በምዕራብ ወለጋ ዞን ለተጠለሉ ወገኖች ድጋፍ የሚውል የቶምቦላ ሎተሪ ሽያጭ እየተካሄደ መሆኑን የዞኑ መንግስት ኮምዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡ የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ወይዘሮ አብዮት ዳንኤል ለኢዜአ እንደገለጹት የቶምቦላ ሎተሪው ከግንቦት 20 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ ለሽያጭ የዋለው በዞኑ 20 ወረዳዎችና ሦስት ከተሞች ነው። ሎተሪው ለሽያጭ በዋለባቸው ባለፉት ሦስት ቀናት ብቻ 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ሽያጭ ለማከናወን መቻሉን ገልጸዋል። ለአንድ ወር በሚቆየው የሎተሪ ሽያጭም ከ23 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ለማግኘት መታቀዱን ነው ኃላፊዋ ያስታወቁት። እንደ ኃላፊዋ ገለጻ የቶምቦላ ሽያጩን በጊምቢ ከተማ በይፋ ለማስጀመር በተዘጋጀ መርሀ ግበር ላይ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ግንባር ቀደም አርሶ አደሮች፣ የወጣት ማህበራት፣ ባለሃብቶችና የመንግስት ሠራተኞች ሎተሪውን በመግዛት የነቃ ተሳትፎ አድርገዋል። የምዕራብ ወለጋ ዞን  ዋና አስተዳዳሪ አቶ ለሊሳ ዋቅወያ በበኩላቸው ለወገን ከወገን በላይ የሚደርስ ባለመኖሩ የዞኑ ነዋሪዎች ለሽያጭ የተዘጋጀውን ቶምቦላ በመግዛት ትብብራቸው እንዲያሳዩ ጥሪ አቅርበዋል። በተመሳሳይ ለተፈናቃዮች ድጋፍ ለማድረግ ሰሞኑን በተደረገ እንቅስቃሴ ለ65 አባውራ ተፈናቃዮች የገንዘብ፣ የቤት ቁሳቁስና አልባሳት ድጋፍ መደረጉን የጊምቢ ከተማ የድጋፉ አሰባሳቢ ኮሚቴ አስታውቋል። የኮሚቴው አስተባባሪ አቶ መልካሙ ታሪኩ እንዳሉት ከ120 ሺህ ብር የሚበልጥ ገንዘብ እንዲሁም ከ340 ሺህ ብር በላይ ግምት ያለው ልብስና የቤት ቁሳቁስ ለተፈናቃዮች ድጋፍ የተደረገ ሲሆን ድጋፉም ከከተማው ነዋሪዎች፣ ባለሀብቶችና ከሙዚቃ ዝግጅት የተሰበሰበ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ከሶማሌ ክልልና አዋሳኝ የኦሮሚያ አካባቢዎች ተፈናቅለው በዞኑ ባቦ ገምቤል ወረዳ መኖር የጀመሩት አቶ ደሊል አህመድ መንግስትና ሕብረተሰቡ ተፈናቃዮችን ለማቋቋም እያደረጉት ላለው ጥረት ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ተከስቶ በነበረው ግጭት በእነሱ ላይ የደረሰው መፈናቀል በሌሎች ላይ እንዳይደገም መንግስት በዘላቂ መፍትሄ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ ጠይቀዋል። ከአራት ቤተሰባቸው ጋር ተፈናቅለው በመንዲ ከተማ የሚኖሩት ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ ጅራታ ከበደ በበኩላቸው በችግር ጊዜ  ከጎናቸው ለቆሙት መንግስትና ህዝብ ምስጋናቸውን አቅርበው በቀጣይ ዘላቂ የሆነ የሥራ እድል እንዲመቻችላው ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም