ከስሜታዊነት ይልቅ በሐሳብ ልዕልናና በምክንያታዊነት የሚመራ ማህበረሰብ መፍጠር ይገባል- ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ

146

አዲስ አበባ መጋቢት 13/2011 ከስሜታዊነት ይልቅ በሐሳብ ልዕልናና በምክንያታዊነት የሚመራ ማህበረሰብ መፍጠር እንደሚገባ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ አሳሰቡ።

ፕሬዘዳንቷ ይህን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ባዘጋጀውና "የኢትዮጵያ አዲሲቷ የተስፋ አድማስ" በሚል መሪ ሃሳብ እየተካሄደ ባለው የውይይት መድረክ ላይ ነው።

ያለፈው አንድ ዓመት በኢትዮጵያ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖሊቲካዊ ታሪክ ያለውን ቦታ የሚገመግምና ለወደፊቱም መንገድ የሚያሳይ የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው፡፡

የለውጥ ሂደቱን ለሁለት ቀናት የሚቃኘው "አዲስ ወግ" የውይይት መድረክ ዛሬ ረፋዱን ተከፍቷል። አዲስ ወግ የመቻቻልና የመከባበር፣ የውይይትና የንግግር ባሕልን የሚያስተዋውቅ አዲስ የሐሳብ ገበያ መድረክ መሆኑም ተጠቅሷል።

ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ "የጉልበትና የአንዱ የበላይነት ዘመኑ አብቅቶ በሐሳብ ልዕልናና በተሻለ አማራጭ ልንመራ ይገባል" ሲሉም ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት "የለውጡን ፈተናዎችና በረከቶች ሁላችንም እየቀመስን ነው" ያሉት ፕሬዝዳንቷ፤ ፈተናዎችን አስወግደን በረከትን ለማብዛት "ከጥላቻ፣ ከጅምላ ፍረጃና ከመነቃቀፍ ፖለቲካ ልንወጣ ይገባልም" ብለዋል።

"የጥላቻ፣ የጅምላ ፍረጃና የመነቃቀፍ ፖለቲካ የሰላምና የስልጣኔ እናት ሆነው አያውቁም፤ በዚህም ከግዴለሽነት ይልቅ ሃላፊነት የሚሰማው ማህበረሰብ መፍጠር የሁላችንም ግዴታ ሊሆን ይገባል" ሲሉም ነው የተናገሩት።

ከመነቃቀፍ፣ ከመፈራረጅ፣ ከመንጋነት የጸዳ ፖለቲካ መፍጠር የሁሉም ድርሻ በመሆኑም ሃላፊነት የሚሰማው ማህበረሰብ ማፍራት የግድ ይለናል ሲሉም ተናግረዋል።

በተለይ ምሁራን የአገሪቷን የመጻኢ እድል መንገድ በማመላከት፣ ስህተትን በማረምና መፍትሄ በማበጀት፣የውይይት ባህል እንዲዳብርና የሃሳብ ልዕልና በህብረተሰቡ ዘንድ እንዲሰርጽ በማድረግ ረገድ ትልቅ ሚና እንደሚጠበቅባቸውም ፕሬዘዳንቷ አሳስበዋል።

ፍትህና ዴሞክራሲ ሊጎለብት የሚችለው ስህተቶችን ነቅሶ የሚያወጣና ትክክለኛውን አካሄድ የሚያሳይ ምሁራን ሲኖሩ ነው ያሉት ፕሬዘዳንቷ፤ በምክንያታዊነት የሚመራና በውይይት የሚያምን ማህበረሰብ መፍጠርም የባለሃብቱ፣ የምሁራንና የሁሉም ማህበረሰብ ድርሻ ነው ብለዋል።

በውይይቱ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ጉዞ ታሪካዊ ዳራና ወቅታዊ ተግዳሮቶች ምንድናቸው? እንዲሁም የኢትዮጵያ የውጭ ፖሊሲና የአፍሪካ ተሳትፎ በሚሉ መነሻ ሃሳቦች ጽሁፎች ቀርበው ውይይት የሚደረግ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም