አሁንም ልዩ ትኩረት የሚሻው ፕሮሶፒስ ጁሊፍሎራ የተባለ መጤ አረም

58
አዲስ አበባ ግንቦት 23/2010 ፕሮሶፒስ ጁሊፍሎራ በ1970ዓ.ም አካባቢ በመካከለኛው አዋሽ አሚባራ ወረዳ ለአፈርና ውሃ ጥበቃ በሚል ምከንያት በተሰራው ቦታ እንደገባ ይነገራል። በአፋር ክልል ከሁለት ዓመት በፊት የተደረገ ጥናት 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዚሁ አረም እንደተወረረና ዓመታዊ የመስፋፋት ሽፋኑም ከ20 ሺህ እስከ 50 ሺህ ሄክታር መሬት እንደሚደርስ ይጠቁማል። መጤ አረሙ ቀድሞ ከሚታወቅበት አፋር ክልል በተጨማሪ በሶማሌ፣ ኦሮሚያና ደቡብ ከልል አርብቶ አደር ወረዳዎች እየተስፋፋ ነው። የእንሰሳት የግጦሽ ሳርና ውሃ ህይወቱ ለሆነው አርብቶ አደር ፕሮሶፒስ ቀድሞ በቀላል ቁፋሮ ይገኝ የነበረውን ውሃ በማድረቅና የግጦሽ መሬትን በማሳጣት ፈተና እንደሆነባቸው ይናገራሉ። በደቡብ ኦሞ ዞን ኛንጋቶም ወረዳም አረሙ ከ27 አመታት በፊት በኬንያ ወታደሮች አማካኝነት እንደገባ እና በቅርብ ጊዜ ፍጥነቱን ጨምሮ በወረዳው ከሚገኙ ቀበሌዎች በሰባቱ ከ300 እስከ 400 ሄክታር መሬት እንደወረረ እና ለኑሯቸው ፈተና እንደሆነ ይናገራሉ። አቶ ሎታሎ ሎኩጃ እንዳሉት “በፊት ውሃ በቀላሉ ማግኘት እንችል ነበር፤ አሁን ብዙ ቆፍረን እንኳን ማግኘት አንችልም። ለከብቶቻችን ሳርና ውሃ ፍለጋ ኬንያ ድንበር ደረስ እየሄድን ለግጭት እየተዳረግን ነው'' ነው ያሉት፡፡ ዛፉ አካባቢው ወሮታል፤ ለመመንጠር ሞክረን ነበር ግን ከአቅማችን በላይ ሆኗል መንግስት እንዲረዳን አንፈልጋለን'' ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ሎኩ ላኔ ናቸው፡፡ የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ሎቶሩሲ ካሬ በበኩላቸው የሳርና የእርሻ መሬት አካባቢ የነበሩ በሙሉ በቸረሙ ብቻ መሸፈኑን ገልጸው፤በዚያ ተጠቃሚ የሆኑ ሰዎቹ ሁሉ መልሰው የመንግስትን ድጋፍ ብቻ የመጠበቅ ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ አረሙ ሁሉንም የአየር ንብረቶች ተቋቁሞ መስፋፋት የሚችል፣ ስሩ ረጃጅም በመሆኑ የከርሰ ምደር ውሃን አሟጦ የሚጠቀምና ከእንስሳት ፅዳጅ ጋር በቀላሉ የሚራባ በመሆኑ መስፋፋቱን ቀጥሏል። በግብርናና እንስሳት ሀብት ሚኒስቴር የአርብቶ አደርና ልዩ ድጋፍ ዳይሬክቶሬት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ አዲስ ስሜ አሁን በአፋር ካሉ 32 ወረዳዎች 20 ወረዳዎች እንዲሁም፣ በሶማሌ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ ህዝቦች ክልል አርብቶ አደር አካባቢዎች ተከስቷል ይላሉ። በሰው ኃይል የሚደረገው አረሙን የማጥፋት ስራም ቀላል አልሆነም ያሉት ባለሙያው፤ በተደጋጋሚ ከሚከሰተው ድርቅ ጋር ተያይዞ "የግጦሽ መሬትን ምርትና ምርታማነት በከፍተኛ ሁኔታ እየቀነሰ ነው፤ በመሆኑም ለአርብቶ አደሩ ፈተና ሆኗል" ብለዋል። አረሙን ለመቆጣጠርና ለመከላከል በሚኒስቴሩ አዲስ ስትራቴጂ ተቀርፆ ወደ ስራ እየተገባ መሆኑንም ይናገራሉ አቶ አዲስ። ስትራቴጂው አረሙ ብዙ ባለመታወቁ እያስከተለ ያለውን ጉዳት ለመቀነስ እና አገራዊ አጀንዳ ለማድረግ ያለመ ነው ብለዋል። አረሙ የሚገኝባቸውን አካባቢዎች ከመለየት ጀምሮ አረሙን የመከላከልና አገልግሎት ላይ በማዋል የመቆጣጠር ስራዎች ይሰራሉ ብለዋል። ከዚህ በፊት በሰው ኃይል ሲደረጉ የነበሩ ሙከራዎች ከአረሙ ተስፋፊነትና ከመሬቱ ሰፊነት አንፃር የሚቻል ባለመሆኑ ከእጅ መሳሪያዎች ጀምሮ ትላልቅ መሳሪያዎችን በመጠቀም ማስወገድ ከተያዙት የስትራቴጂው አማራጮች ተካተዋል። ሌላኛው የስትራቴጅው አካል አረሙን ለፋብሪካ ግብዓትነትና ለሌሎች አገልግሎቶች በመጠቀም መቆጣጠር መሆኑን አቶ አዲስ ይናገራሉ። በዚህም የህንድ ባለሀብቶች በአፋር አካበቢ ለፋብሪካ ግብዓትነት ለመጠቀም ከኢንቨስትመንት ኮሚሽን ፍቃድ ወስደው ከህብረተሰቡ ጋር እየተወያዩ ነው ብለዋል። ስራውን በተቀናጀ መልኩ ለማከናወንም በፌዴራል ደረጃ ከግብርናና እንሰሳት ሀብት ሚኒስቴር፣ ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና ከግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የሚሳተፉበት ሴክሬታሪያት ይቋቋማል ብለዋል። እንደ አቶ አዲስ ገለፃ ስተራቴጂው በሁለት ክልሎች በአፋር ብሄራዊ ክልልና በሶማሌ ክልል ለባለ ድርሻ አካላት የማስተዋወቅ ስራም ተሰርቷል። ይህ በጀት ዓመት ከመጠናቀቁ በፊትም በኦሮሚያ እና በደቡብ ህዝቦች ክልል የማስተዋወቅ ስራ ይሰራል። ለባለ ድርሻ አካላት የማስተዋወቅ ስራ እንደተጠናቀቀም ትኩረት እንዲደረግባቸው በአረሙ የተወረሩ ቦታዎቸን ልየታ ስራ ይሰራል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም