የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ጽንፍ ከወጣው የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ሊታቀቡ ይገባል--የሚዲያ ባለሙያዎች

162

አዲስ አበባ መጋቢት 13/2011 የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ጽንፍ ከወጣው የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ሊታቀቡ እንደሚገባ ተጠቆመ።

በመደበኛዎቹ ሚዲያዎች በተለይም ህዝብን በማገልገል ትልቅ ኃላፊነት ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሚያስተላልፏቸው መልዕክቶችም የተዛቡና ቅራኔ የሚፈጥሩ እንዳይሆኑ ጥንቃቄ እንዲያደርጉም ተጠይቋል።

በአገራችን ኢትዮጵያ የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣ ሲሆን 97 በመቶ የሚሆነው የኢንተርኔት ተጠቃሚ የፌስቡክ ተጠቃሚ እንደሆነም ነው ጥናቶች የሚያመላክቱት።

ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመጣው የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም በተለይም የፌስቡክ ገጽ በበርካቶች ዘንድ ሃላፊነት የጎደለው፣ ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጩና አገርንም የሚጎዱ መልዕክቶች ሲተላለፉ ይስተዋላል።

ማህበራዊ ሚዲያ መረጃን በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች በቀላሉ ለማድረስ ሁነኛ ድልድዮች ቢሆኑም ያንን በተገቢው አለመጠቀም ግን ጉዳቱ የከፋ ሊሆን እንደሚችል የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ገልጸዋል።

በተለይም የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በማህበረሰቡ ዘንድ ካላቸው ተቀባይነት አንጻር ከሙያዊ ሥነ-ምግባር ውጪ የሆነና ጽንፍ የያዘ አዘጋገብም ሆነ የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም በአገርና በህዝብ ላይ የሚያስከትለውን አሉታዊና አዎንታዊ ተጽእኖ የጎላ እንደሆነ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትጋዜጠኛ ድልነሳ ምንውዬለት በሰጠው አስተያየት" ከኢቲክሱ ውጪ ስራዎች በሚሰሩበት ሰዓት ከፍተኛ ጉዳት ነው የሚያደርሰው፤ ሚዲያ እንደ 4ኛ መንግስት እየተባለ ነው የሚያዘው፤ ስለዚህ በሚዲያዎች በኩል የሚተላለፉ መረጃዎች ሚዛናዊነታቸውን የሚጠብቁና ትክክለኛ የማይሆኑ ከሆነ ወደ ህብረተሰቡ በሚደርሱ ሰዓት ከፍተኛ ችግር ይፈጥራሉ፤ ስለዚህ ይሄ በጣም መስተካከል ያለበት ጉዳይ ነው"

"እንደ ማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል ሃሳቡን በነጻነት ሲናገር፣ ሲገልጽ፣ ሲያንሸራሽር ታያለህ፤ ነገር ግን እኛ ጋዜጠኞች ደግሞ ከህብረተሰቡ የምንቀበለውን ሃሳብ ወይም ገለጻ በምን መልኩ ነው ማቅረብ ያለብን? ምክንያቱም አንድ ጋዜጠኛ ብዙ ነገር ሊናገር ይችላል ነገር ግን የሚናገረው ነገር ለህብረተሰቡ እንዴት ነው ማድረስ ያለበት ጋዜጠኛው የሚለውን ኢቲክሱን ጠብቆ ማቅረብ መቻል አለበት "   በማለት የተናገረውየሪፖርተር ጋዜጣ ጋዜጠኛ ታምሩ ጽጌ ነው፡፡

"የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በሚሰሩበት ሚዲያ ላይ የሚጽፉት፣ የሚዘግቡት ሌላ፤ ከዚያ መለስ ደግሞ በግል የፌስቡክ ገጻቸው ላይ ተቃራኒ የሆነ ነገር ይጽፋሉ ይሄ አንዳንዴ ካለማወቅ ነው ሌላ ጊዜ ደግሞ ሆን ብሎ የሚደረግ ይመስለኛል። ስለዚህ አንድ ጋዜጠኛ የሚጽፈው በህብረተሰቡ ዘንድ ትልቅ ተዓማኒነት አለው፤ ጋዜጠኛ ኢንስቲትዩሽኑን ወክሎ የሚሰራ ስለሆነ በአንድም በሌላም የሚጽፈው ነገር ከፍተኛ ኢምፓክት አለው፤ ይሄንን በአግባቡ መረዳት ያስፈልጋል"  ያሉትበኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የኦንላይን ሚዲያና ፕሮዳክሽን ዘርፍ ስራ አስኪያጅ አቶ አርአያ ጌታቸው ናቸው፡፡

ጋዜጠኝነት እንደ ሌላው የሙያ ዘርፍ የራሱ የሆነ ስነ-ምግባርና መርህ ያለው ሲሆን በዋነኛነት ደግሞ ገለልተኛነቱን ጠብቆ ማገልገል እንዳለበት የሚገልጹት ባለሙያዎቹ፤ ለየትኛውም አካል ባለመወገን ሃቅን በማውጣት ላይ የተመሰረተ ስራ መስራት ተገቢ መሆኑን በአጽንኦት ያነሳሉ።

ለዚህም በተለይ ጋዜጠኞች የፕሬስ ነጻነታቸውንና መብታቸውን ሊገድብ በማይችል መልኩ ዘገባዎችን እንዲሰሩ የሚዲያ ተቋማት በባለሙያዎቻቸው ላይ ከፍተኛ ስራ መስራት አለባቸው ነው ያሉት።

ጋዜጠኛ ድልነሳ ምንውዬለት ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በበኩላቸው "የፕሬስ ነጻነት ቢኖርም ነጻነቱ መሆን ያለበት መዘገብ  ያለብንን እንደጋዜጠኛ ነጻ ሆነን ያለምንም መሸማቀቅ ነው እንጂ አድሎአዊነት ባለው መንገድ፣ ገጽታን በሚያበላሽ፣ በህዝቦች መካከል መቃቃርን ሊያመጣ በሚችል መንገድ የምናገኘውን ነገር ሁሉ እንድንዘግብ አይደለም መሆን ያለበት ጋዜጠኛ ከፕሬስ ነጻነት አዋጁ የተሰጣቸውን መብት ሊገድብ በማይችል መልኩ ዘገባዎችን እንዲሰሩ ተቋማት የራሳቸውን ስራ መስራት አለባቸው" ብለዋል፡፡

"እንደ ኢትዮጵያውያን ምንድነው የሚያስፈልገን የሚለውን ማሰብ አለብን የሚሉት የካፒታል ጋዜጣ ጋዜጠኛ ተስፋዬ ጌትነት  ይህቺ ደሃ አገር ናት በጣም ብዙ የሚራቡ ሰዎች ያሉባት፣ ብዙ ስራ አጥ ያለባት፣ ብዙ ወጣቶች የሚሰደዱባት አገር ናት  ይህቺ አገር ምን ያስፈልጋታል? ምን ብጽፍ ነው መፍትሄ የሚያመጣው ካልሽ አእምሮሽ ሰላምን፣ ልማትን የሚያመጡ ነገሮች ላይ  ማተኮሩ ጠቃሚ ነው" ብለዋል፡፡

በአገሪቷ የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም የራሱ የሆነ የህግ ማዕቀፍ እንዲኖረውና ቁጥጥር በማድረግ ረገድም መንግስት ሃላፊነቱን መወጣት እንደሚገባውም ጠቁመዋል። 

በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት 4 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ እንደሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም