የኢንዶኔዥያው አየር መንገድ በ6 ቢሊዮን ዶላር ለመግዛት ያዘዘውን ቦይንግ 737 ማክስ እንዲሰረዝለት ጠየቀ

89

አዲስ አበባ መጋቢት 13/2011 በኢንዶኔዥያ የሚገኘው ጋሩዳ አየር መንገድ ከቦንይግ ኩባንያ በ 6 ቢሊዮን ዶላር ለመግዛት ያዘዛቸውን የቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን ግዥ እንዲሰረዝለት ጠየቀ።

አየር መንገዱ ለኩባንያው በላከው ደብዳቤ የ49 ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላኖች ግዥ ትዕዛዝ እንዲሰረዝለት መጠየቁን የአየር መንገዱ የፋይናንስ ኦፊሰር ፉአድ ሪዛል ለሮይተርስ ተናግረዋል።

ትዕዛዙ 6 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ የሚያወጡ የቦይንግ 737 አውሮፕላኖችን ለመግዛት የተደረገ ቢሆንም እሱን በመተው በምትኩ ሌሎች የቦይንግ ሞዴሎችን ለመግዛት በመደራደር ላይ መሆኑንም ኦፊሰሩ ተናግረዋል።

ጋሩዳ አየር መንገድ ትዕዛዙ እንዲሰረዝለት እቅድ እንዳለው በይፋ በመጠየቅ ቀዳሚው ሆኗል።

የመሰረዙ ምክንያት ደግሞ በቅርቡ በኢትዮጵያ ተከስክሶ የ157 ሰዎችን ህይወት የቀጠፈው የቦይንግ 737 ማክስ 8 አደጋ ነው።

በኢንዶኔዥያ የሚገኘው ተቀናቃኙ ላየን አየር መንገድም  በጥቅምት ወር የተከሰከሰበትን ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላንን መነሻ በማድረግ የሰጠውን ትዕዛዝ ለማጠፍ እያሰበበት መሆኑ ተጠቅሷል።

የጋሩዳ አየር መንገድ ስራ አስፈጻሚ አሪ አሽካህራ ባለፈው ሳምንት እንደተናገሩት "ደንበኞች በቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን ላይ እምነት አጥተዋል"።

መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም በበረራ ቁጥር ET- 302 ወደ ኬንያ ሲያመራ የነበረው ቦይንግ ሰራሹ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን ተከስክሶ ለ 157 ሰዎች ሕልፈት ምክንያት መሆኑን ተከትሎ አምራች ኩባንያውን ጨምሮ ከ50 በላይ የሚሆኑ የዓለም ሀገራት አውሮፕላኑን ከበረራ ማገዳቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም