ወጣቶች 5 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር የሚገመት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጥተዋል

456

አዳማ መጋቢት 13/2011 ወጣቶች ባለፉት ስድስት ወራት 5 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር የሚገመት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መስጠታቸውን የሴቶች፣ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

በሚኒስቴሩ የስትራቴጂካዊ ሥራ አመራር ዳይሬክቶሬት ተወካይ አቶ በሽር ሳሃሊ ለኢዜአ እንዳስረዱት ሦስት ሚሊዮን የሚሆኑት ወጣቶቹ  አገልግሎቱን ለኅብረተሰቡ የሰጡት ዕውቀታቸውንና ጉልበታቸውን በማስተባበር ነው።

ወጣቶቹ በአገሪቱ ሰላም እንዲሰፍንና ለውጡን በማስቀጠል አስተዋጽኦ ማድረጋቸውንም አመልክተዋል።

በተለይም ከሰባት ክልሎች ተውጣጥተው በወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተሳተፉ  አንድ ሺህ ወጣቶች አብሮነት፣መቻቻልና መከባበርን የተማሩበትና ያስተማሩበት በጎ ተግባር ፈጽመዋል ብለዋል። 

በሥነ ተዋልዶ ጤና፣በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር፣በአሉታዊ መጤ ባህሎችና አደንዛዥ እፅ ዙሪያ ለወጣቶች ትምህርት  መሰጠቱንም  አቶ በሽር ተናግረዋል።

በተጨማሪም በአረጋውያን እንክብካቤ፣በማጠናከሪያ ትምህርት፣በተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ፣በከተሞች ፅዳትና ውበት፣በወጣቶች ስብዕና ግንባታ ልማት ተሳትፈው የመንግሥትና የሕዝብ ወጪ ማዳናቸውን አስታውቀዋል፡፡

ወጣቶች የተሟላ ስብዕና እንዲኖራቸው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አንዱ ማሳያ ነው ያሉት ደግሞ የኦሮሚያ ወጣቶች ፌዴሬሽን የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ወጣት ለማ በቀለ ነው።

በክልሉ ከአራት ሚሊዮን በላይ ወጣቶች የአረጋውያን የፈረሱ ቤቶችን በመጠገንና በማደስ፣አልባሳትና ቁሳቁስ በማሰባሰብ ከማሳካት አንፃር ሰብዓዊ ድጋፍን ያካተተ አገልግሎት መስጠታቸውን ገልጿል።

የአዳማ ከተማ ወጣቶች ማህበር የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ወጣት እሱባለው ግርማ በበኩሉ የከተማው ወጣቶች  ከበጎ ፈቃድ አገልግሎት በተጓዷኝ በተለይም በከተማዋ ሰላም ለማስፈን ሚና ተጫውተዋል የብሏል።

የአረጋውያንን ቤቶች  እድሳትና ጥገና ፣ለወላጅ አልባና አቅም የሚያንሳቸው ከ800 በላይ ተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስ እንዲያገኙ እገዛ  መደረጉን  አስታውቋል።