የእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ዙር ውድደር ነገ በሚደረጉ ጨዋታዎች ይጠናቀቃል

61

አዲስ አበባ መጋቢት 13/2011 የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ  በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ነገ በሚደረጉ ተስተካካይ ጨዋታዎች ይጠናቀቃል።

10 ክለቦች እየተሳተፉበት የሚገኘው የእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያው ዙር ውድድር ታህሳስ 27 ቀን 2011 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን ነገ በሚካሄዱ ጨዋታዎች የሚጠናቀቅ ይሆናል።

በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም መከላከያ ከድሬዳዋ ከተማ ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት ላይ፤  ፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ከፌዴራል ፖሊስ ከረፋዱ አራት ሰዓት ከ30 ደቂቃ ላይ ይጫወታሉ።

ዱራሜ ላይ ከምባታ ዱራሜ ከፕሪሚየር ሊጉ መሪ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ጋር ከረፋዱ አምስት ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።

ከትናንት በስቲያ በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም መቐለ ሰብዓ እንደርታ ከጎንደር ከተማ ጋር ባደረጉት ተስተካካይ ጨዋታ መቐለ ሰብዓ እንደርታ 24 ለ 22 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።

የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ በ16 ነጥብ ሲመራ፤ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ በ15 ነጥብ፣ መቐለ ሰብዓ እንደርታ በ13 ነጥብ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል።

እስካሁን በፕሪሚየር ሊጉ ምንም ጨዋታ ያላሸነፈው ጎንደር ከተማ ያለ ምንም ነጥብ 10ኛ ደረጃን ይዟል።

የ2011ዓ.ም የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ሶስተኛው የውድድር ዓመቱ ነው።

ፕሪሚየር ሊጉ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ በመካሄድ ላይ ሲሆን፤ መከላከያ በ2009 ዓ.ም እንዲሁም ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ያለፈው ዓመት የሊጉ አሸናፊ መሆናቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም