የነቀምቴ አውሮፕላን ማረፊያ አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ተጠቆመ

303

የነቀምቴ መጋቢት 13/2011 የነቀምቴ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታን ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎች ገለፁ።

ከሁለት ዓመት በፊት የተጀመረው የአውሮፕላን ማረፊያው ግንባታ ሥራ 40 በመቶ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተነግሯል።

የአየር መንገዱ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አስራት በጋሻው ለኢዜአ እንደገለፁት 748 ሚሊዮን ብር በጀት ተይዞለት የተጀመረው ግንባታ መጠናቀቅ ከነበረበት ጊዜ በስድስት ወር ዘግይቷል።

“በወሰን ማስከበር፣ በሥራ ተቋራጭ ድክመትና በአካባቢው ተከስቶ በነበረ የፀጥታ ችግር ምክንያት ግንባታው በወቅቱ ሳይጠናቀቅ ቀርቷል” ብለዋል ።

በአካባቢው አንጻራዊ ሰላም በመስፈኑና ሌሎች ችግሮች በመፈታታቸው የተጓተተው ግንባታ እንዲፋጠን በመደረግ ላይ መሆኑን ተናግረዋል ።

በአየር መንገዱ የግንባታ ፕሮጀክቱ ተቆጣጣሪ ማሐንዲስ አቶ ብሩከ ከበደ በበኩላቸው የአውሮፕላን ማረፊያ ሜዳና የሦስት ኪሎ ሜትር ማኮብኮቢያ የአፈር ሙሊት ሥራ ተጠናቆ ጠጠርና አስፓልት እየለበሰ መሆኑን ተናግረዋል ።

በኢፌዴሪ መከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ የነቀምቴ አውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር ማሩ ግዛቸው ግንባታውን አንድ አመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ በሙሉ አቅም እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

“በግንባታው ከ600 የሚበልጡ የአካባቢው ነዋሪዎች የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል” ብለዋል ።

በአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታው ሥራ በተመረቀበት የቅየሳ ሙያ ተቀጥሮ እየሰራ መሆኑን የገለጸው ደግሞ ወጣት ሃብታሙ እሸቴ ነው።

በ200 ሄክታር መሬት ላይ ግንባታው እየተካሄደ ያለው የነቀምቴ አውሮፕላን ማረፊያ 45 ሜትር ስፋትና 3 ነጥብ 1 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ማረፊያና ማኮብኮቢያ አስፓልት ኮንክሪት ያለው መሆኑ ታውቋል ።