ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ስምምነትን ማጽደቋን የአፍሪካ ህብረት አደነቀ

110

አዲስ አበባ መጋቢት 13/2011 ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ስምምነት ማጽደቋን የአፍሪካ ህብረት አደነቀ።

ኢትዮጵያን ጨምሮ በአህጉሪቷ የሚገኙ 21 አገራት ስምምነቱን በማጽደቅ የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና እውን እንዲሆን ሚናቸውን ተወጥተዋል።

የአፍሪካ ህብረት የንግድና ኢንዱስትሪ ኮሚሽነር አልበርት ሙካንጋ በትዊተር ገጻቸው ኢትዮጵያ ስምምነቱን ማጽደቋን በማድነቅ "ውሳኔው ጊዜውን የጠበቀና ታሪካዊ ነው" ብለዋል።

"የአንድ ተጨማሪ ፓርላማን ማረጋጋጫ ካገኘን ስምምነቱን ተግባራዊ እናደርጋለን" በማለትም ኮሚሽነሩ መናገራቸውን አፍሪካ ኒውስ በድረገጹ ጠቅሷል።

ባለፈው ዓመት ሩዋንዳ ላይ የተሰባሰቡ 44 የአፍሪካ ህብረት አባል አገራት ስምምነቱን በተመለከተ ውሳኔ ያሳለፉ ሲሆን ስምምነቱን ወደ ተግባር ለማስገባት ደግሞ የ 22 አገራት የህግ አውጭውን ምክር ቤት ይሁንታ ያስፈልጋል።

ስምምነቱ ተግባራዊ መደረግ ከጀመረ በዓለም ላይ ትልቁ የንግድ ቀጠና ይሆናልም በማለት ገልጸዋል።

አጋርነቱ እ.አ.አ በ2022 በአፍሪካ አገሮች መካከል ያለውን የንግድ ልውውጥ በ 52 በመቶ በማሳደግ በመካከላቸው ያለውን የሸቀጦች የንግድ ታሪፍ በ 90 በመቶ ያስቀራልም ተብሎለታል።

እንዲሁም አገልግሎቶችን ነጻ በማድረግና በእርስ በርስ የንግድ ልውውጥ ሂደት የሚታዩ ሌሎች መሰናክሎችን በማስወገድ በተለይም በድንበር ላይ የሚደረገውን አሰልቺ ቁጥጥር በማሳጠር አገራቱን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትናንት ባካሄደው 27 መደበኛ ጉባዔው የአፍሪካን ነጻ የንግድ ቀጠና ማጽደቁ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም