የአየር ንብረት ለውጥ ስራዎችን በልማታዊ ሴፍትኔት መርሃ ግብር የማካተት ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ

47

አዳማ መጋቢት 12/2011 በግብርና ሚኒስቴር የተዘጋጀውና ከአውሮፓ ህብረት በተገኘ  ድጋፍ ተግባራዊ የሚሆን  የአየር ንብረት ለውጥ ስራዎችን በልማታዊ ሴፍትኔት መርሃ ግብር የማካተት ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ።

ፕሮጀክቱ ዛሬ በአዳማ ከተማ ይፋ  በሆነበት መድረክ እንደተገጸለው ስራው  ከአውሮፓ ህብረት በተገኘ ስምንት ሚሊዮን ዶላርና የቴክኒክ ድጋፍ ተግባራዊ የሚደረግ ነው፡፡

በዚህ ወቅት የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ካባ ኡርጌሳ እንዳስታወቁት ፕሮጀክቱ የምግብ ዋስትና ችግር ጎልቶ በሚታይባቸው 350 የሀገሪቱ ቆላማ ወረዳዎች እንደ አውሮፓ አቆጣጠር  ከ2019 ጀምሮ  ለአራት ዓመታት ተግባራዊ የሚደረግ ነው።

የደን ልማት፣አካባቢን ለአደጋ በማያጋልጥ መልኩ የመስኖ ልማት ስራዎችን ማስፋፋትና የገበያ ትስስር መፍጠር፣ የሰውና የእንስሳት መጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ውሃ ማቆር ከፕሮጀክቱ ስራዎች መካከል ይገኙበታል፡፡

የገጠር መንገድ መሰረተ ልማትና የትምህርት ተቋማትን ማሻሻል ስራዎችም ተመልክተዋል።

በፕሮጀክቱ መርሃ ግብር ችግር ባለባቸው ስፍራዎች የሚገኙ ዜጎች ከጠባቂነት ይልቅ አካባቢያቸውንና እራሳቸውን ለመለወጥ በሚያስችሏቸው ማህበረሰብ አቀፍ ሥራዎች እንዲሳተፉ ይደረጋል።

የምግብ ዋስትና ችግር  በሚጎላባቸው አካባቢዎች አርሶና አርብቶ አደሩ በተፋሰስ ልማት እና በአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች በመሳተፍ ከተረጂነት እንዲላቀቅ ጥረት እንደሚደረግ ሚኒስትር ዴኤታው አስረድተዋል።

ለፕሮጀክቱ የተመደበውን ሀብት በአግባቡ ጥቅም ላይ በማዋል ህብረተሰቡ  ተጠቃሚ እንዲሆን አስፈጻሚ አካላት በትኩረት መንቀሳቀስ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በሚኒስቴሩ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም ዳይሬክተር አቶ ተፈራ ታደሰ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ በምግብ እራሳቸውን ለመቻል ችግር የገጠማቸውን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ነዋሪዎችን ህይወት ለማሻሻል ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

የተፋሰስ ስራው ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር መላመድና መጣጣሙን ማረጋገጥ የፕሮጀክቱ ዓላማ እንደሆነ አመልክተዋል።

የልማታዊ ሴፍቲኔት መርሃ ግብሩ በአውሮፓ ህብረት የፋይናንስ ድጋፍ ሲደረግ የአሁኑ ለአራተኛ ጊዜ መሆኑን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡

ባለፉት 15 ዓመታት አርሶና አርብቶ አደሩን በማህበረሰብ አቀፍ ሥራዎች በማሳተፍ በቀጥታና የምግብ ድጋፍ ተጠቃሚዎች እንዲሆኑ ሲደረግ መቆየቱን አስታውሰዋል።

ፕሮጀክቱን ይፋ ለማድረግ በተዘጋጀው መድረክ ተግባራዊ የሚሆኑባቸው ክልሎች ፣ የአውሮፓ ህብረት ተወካዮችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም