ለኦፓል ማዕድን አምራቾች ምቹ የገበያ ለመፍጠር የሚያስችል ማዕከል ሊከፈት ነው

491

አዲስ አበባ መጋቢት 12/2011 በአማራ ብሔራዊ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን በኦፓል ማዕድን አምራችነቷ በምትታወቀው ደላንታ ወረዳ የኦፓል ምቹ የገበያ ትስስር ለመፍጠር የሚያስችል የገበያ ማዕከል በሙከራ ደረጃ ሊከፈት መሆኑን የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስቴሩ ዛሬ በደላንታ ወረዳ በሚገኙ የኦፓል ማዕድን አምራቾችና በኦፓል ላኪዎች መካከል የገበያ ትስስርን ለመፍጠርና ህገ ወጥ የማዕድን ንግድን ለማስቀረት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የውይይት መድረክ አዘጋጅቷል።

የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትር ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ በዚህ ወቅት እንደተናገሩት፣ ለከበሩ ማዕድናት ምርት ገበያ ባለመፈጠሩ የተነሳ አገሪቱ ከዘርፉ የምታገኘው የውጭ ምንዛሬ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መጥቷል።

የከበሩ ማዕድናት አምራቾች በቀጥታ ከግብይት ጋር መገናኘት ካለመቻላቸው ባሻገር በመሃል ያሉ ሰንሰለቶች ምክንያት የአገር ሃብት እየባከነ መሆኑን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

በኦፓል ግብይት ላይ የሚያጋጥመውን ሰንሰለት ለማሳጠር ምርቱ በሚገኝበት ደላንታ ወረዳ አምራቹን ከገበያው ጋር በቀጥታ የሚያገናኝ የገበያ ማዕከል መጋቢት 30 ቀን 2011 ዓ.ም በወረዳው ውስጥ እንደሚከፈት ገልጸዋል። የገበያ ማዕከሉ ውጤት ታይቶ በሌሎች የከበሩ ማዕድን አምራች አካባቢዎችም ሌሎች ማዕከላት እንደሚከፈቱ ጠቁመዋል።

በባህላዊ መንገድ እየተመረተ ያለውን የኦፓል ማምረት ስራ በቴክኖሎጂ በማገዝ ዘመናዊ እንዲሆን ለማድረግ አምራቾች ስልጠና እንዲያገኙ የሚደረግ መሆኑን ጠቁመዋል።

አንድ ኪሎ ግራም ኦፓል በጥሬው 6ሺህ እሴት ተጨምሮበት ደግሞ 40 ሺህ ዶላር እንደሚሸጥ የተናገሩት ሚኒስትሩ እሴት ጨምሮ ለገበያ ማቅረብ ትኩረት እንደሚሰጠው አመልክተዋል።

የደላንታ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ አርጋው ጌታቸው በበኩላቸው የኦፓል ማዕድን ገበያ በህጋዊ መንገድ ባለመመራቱና የደላላ ጣልቃ ገብነት ያለው በመሆኑ አምራቾች ተገቢውን ጥቅም እያገኙ እንዳልሆነ ገልጸዋል።

ይህንን ችግር ለመፍታት እንዲቻል ወረዳው ለሚኒስቴሩ ጥያቄ አቅርቦ እንደነበር አስታውሰዋል።

የገበያ ማዕከሉን በወረዳው ለመክፈት መወሰኑ የህገ ወጥ ደላሎችን ሰንሰለት የሚቆርጥ መሆኑን በመግለጽ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በደላንታ ወረዳ በህጋዊ መንገድ 27 የኦፓል አምራች ማህበራት ያሉ ሲሆን የተሻለ አሰራር እንዲኖርና በህጋዊ መንገድ እንዲመሩ በድጋሚ የማጥራት ስራም እንደሚሰሩ የወረዳው አስተዳዳሪ አክለዋል።

የኢትዮጵያ የከበረ ማዕድናት የላኪዎች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ አበበ ከዚህ በፊት የኦፓል ምርት በህጋዊ መንገድ ለላኪዎች እንደማይደርስ ገልጸው የገበያ ማዕከል መከፈቱ ችግሩን ሊፈታ እንደሚችል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

በባህላዊ መልኩ የሚያመርቱ ብዙ በመሆናቸው የኦፓል ፍርስራሽ ''አጀራ'' የሚባል ምርት ሲኖር በዋጋም ከኦፓሉ የሚያንስ ስለሆነ ይህን እየባከነ ያለውን ማዕድን ለመታደግ በስልጠና የተደገፈ አሰራር ይዘረጋል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም