በትግራይ በተካሄደው ክልል አቀፍ የቼዝ ውድድር ሸራሮ ከተማ አሸናፊ ሆነ

95

መቀሌ መጋቢት 12/2011 በትግራይ  ለመጀመሪያ ጊዜ በተካሄደው ክልል አቀፍ የቼዝ ውድድር  የሸራሮ ከተማ በሁለቱም ጻታ አሸናፊ ሆነ።

ከመጋቢት ስድስት እስከ 12 በመቀሌ ከተማ በተካሄደው በዚሁ ውድድር ሸራሮ ከተማ በሁለቱም ጾታ አሸናፊ በመሆን ሁለት ዋንጫዎችን  በብቸኝነት መውሰድ ችሏል።

የሽሬ እንዳስላሴና በመቀሌ የሓድነት ክፍለ ከተማ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃ ይዘው ውድድራቸውን አጠናቀዋል፡፡

በክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ቢሮ የቼዝ ፌዴሬሽን ባለሙያ አቶ ካህሳይ ፍሰሃ እንዳሉት በክልሉ የሚገኙ ወረዳዎችንና የከተማ አስተዳደሮችን በመወከል 100 ተወዳዳሪዎች ተሳትፈዋል፡፡

ከሚያዝያ 5 እስክ  ሚያዝያ 16 ቀን 2011 ዓ.ም. አዲስ አበባ በሚካሄደው ሀገር አቀፍ የቼዝ ውድድር ክልሉን በመወከል የሚሳተፉ አስር ተወዳዳሪዎች መመረጣቸውን አስታውቀዋል።

ሸራሮ ከተማን በመወከል የተሳተፈውና ኮኮብ ተወዳዳሪ በመሆን ክልሉን ወክለው በሀገር አቀፍ ውድድር ከተመረጡት መካከል ወጣት  ሮቤል ብርሃነ አንዱ ነው።

በቼዝ ውድድር ሀገራቸውን ለማስጠራት የሚችሉ ተወዳዳሪዎችን ለማፍራት ለዘርፉ የተሻለ ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡

የሽሬ እንዳስላሴ ከተማን በመወከል ሴት ኮኮብ ተወዳዳሪ የሆነችው ወጣት ሲሳይ ገብረእግዚአብሔር በበኩሏ በቼዝ የተደራጁ  ክለቦች መኖር  ዘርፉን ለማሳደግ እንደሚያስችል ተናግራለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም