ባለስልጣኑ የሸማቹን መብት ለማስጠበቅ የባለድርሻ አካላትን ድጋፍ ጠየቀ

61

አዲስአበባ መጋቢት 12/2011 የንግድ ውድድር የሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን የሸማቹን መብት ለማስጠበቅ የባለድርሻ አካላትን ድጋፍ እንደሚያስፈልገው ገለጸ።

ባለስልጣኑ ''ጥራት ያለው ምርትና አገልግሎት ለሸማቾች ደህንነት'' በሚል መሪ ሀሳብ የሸማቾች መብት ቀንን በኢትዮጵያ ለስድስተኛ ጊዜ አክብሯል።

በስነ ስርዓቱ ላይ የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ መሰለች ወዳጆ እንደገለጹት፤ የሸማቾችን መብት በማስጠበቅ ረገድ አጋር አካላት የሚጠበቅባቸውን ሚና እየተወጡ አይደለም።

''ሸማች ማህበረሰቡ በሸመታ ወቅት የሚያጋጥመውን ተግዳሮት በከፊልም ቢሆን እንዲቀርፍ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት መስራቱ አስፈላጊ ነው'' ያሉት ወይዘሮ መሰለች ሸማቹ የሚያጋጥመውን ችግር ለመፍታት ከህጋዊ ነጋዴዎች ጋር መገበያየት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በግብይት ወቅት የሚያጋጥምን ጉድለት ለመፍታት የሚቻለው ከህጋዊ ነጋዴ በመሸመት ብቻ እንደሆነ አመልክተዋል።

''የተገዛ እቃ ጉድለት ያለበት እንደሆነ ከተገዛበት ቀን ጀምሮ በ15 ቀናት ውስጥ እቃው እንዲለወጥ ወይም ዋጋው እንዲመለስ የሚያስገድድ የህግ አግባብ አለ'' ብለዋል ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ።

የሸማቹን መብት ለማስጠበቅ የሚያስችሉ የህግ አግባቦች ስላሉ ከህጋዊ ቦታ በመግዛት ዋስትና ያለው እቃ መሸመት እንደሚያስፈልግና ህገወጥ ንግድን መከላከል የሁሉም ጥረት መሆን እንደሚገባው ገልጸዋል።

በንግዱ ዘርፍ አሉታዊ ተጽእኖ እያሳደሩ ያሉ የንግድ አሰራር ግድፈቶችንና የሸማቾች ደህንነትና ጤንነት የሚጎዱና የመብት ጥሰቶችን በመግታት ዘርፍ በነጻ ገበያ ፖሊሲ መርሆች መሰረት ፍትሃዊ የንግድ ውድድር እንዲሰፍን ለማድረግ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ወይዘሮ መሰለች ተናግረዋል።

በተጨማሪም በሸማቹ ላይ ጫና የሚፈጥር አካል ሲኖር በባለስልጣኑ ነጻ የስልክ መስመር 8478 ወይም 8177 ጥቆማ እንዲያደርሱ ጠይቀዋል።

በአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ የንግድ ኢንስፔክሽን ሪጉላቶሪ ዳይሬክተር አቶ ካሳሁን በየነ በበኩላቸው በሸማቾች ላይ የሚደርሱ ማጭበርበሮችን ለመከላከልና ዋስትና የሌላቸው ምርቶች ወደ ገበያ እንዳይገቡ ለማድረግ ህገወጥ ነጋዴዎችን ወደ ህጋዊ መስመር ለማስገባትና እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚሁ ጎን ለጎን ገበያውን ለማረጋጋት እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ሸማቹ እያቀረባቸው ያሉ ቅሬታዎችና ክሶች በህገወጥ ነጋዴዎች የሚፈጸሙ በመሆናቸው ህገወጥ ነጋዴዎችን ወደ ህጋዊ መስመር ለማስገባት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።

''ሸማቹ ህብረተሰብ ህጋዊ ንግድን ማበረታታት ይጠበቅበታል'' ብለዋል።

ህገወጥ ንግድን መከላከል የአንድ ወገን ሃላፊነት ብቻ ሳይሆን የሁሉንም ድጋፍ የሚጠይቅ መሆኑን ገልጸው በተለይም መገናኛ ብዙሃን በስፋት ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም