ከለውጥ አመራሩ ጋር በመሆን ሠላምን እናረጋግጣለን---የአባይ ጮመን ወረዳ ነዋሪዎች

57

ነቀምት መጋቢት 12/2011 ከለውጥ አመራሩ ጋር በመሆን ሠላምን ለማረጋገጥና ልማትን ለማስቀጠል እንደሚሰሩ በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን የአባይ ጮመን ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ።

ነዋሪዎቹ ትላንት በፊንጫ ከተማ ባደረጉት ኮንፈረንስ ላይ እንደገለጹት መንግሥት የሕዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚያደርገው ጥረት ውስጥ የድርሻቸውን ለማበርከት ዝግጁ ናቸው።

አንዳንድ የወረዳው የቀድሞ አመራሮች በህዝቡ ላይ የደረሱት ጫና ለወረዳው ሰላም ችግር መፍጠሩን መንግስት ተገንዝቦ እነሱን በማንሳት ለህዝቡ ይሰራሉ ብሎ ያመነባቸውን አመራሮች ማምጣቱ አግባብ እንደሆነም ተናግረዋል።

አሁን ወደ ሥልጣን የመጣው የለውጥ አመራር የሕዝቡን አደራ ተቀብሎ በእኩልነትና በፍትሃዊነት በማገልገል የተጀመረውን ልማት ማስቀጠል እንዳለበትም ተሳታፊዎቹ አሳስበዋል፡፡

የአባይ ጮመን ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ አብዱላሂ አሜ  እንደተናገሩት ለውጡ ሕዝቡን የሰላሙና የልማቱ ተጠቃሚ ለማድረግና የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የሚያግዝ ነው።

በወረዳው ሕዝቡን የበደሉ አመራሮች በፈጸሙት ግፍና በደል ተጠያቂ  እንደሚሆኑ ገልጸው ነዋሪው የተገኘውን አንፃራዊ ሰለላም በመጠቀም ያለምንም ሥጋት ከመንግሥት ጎን ሆኖ ልማትን ለማስቀጠልና ሠላምን ለማረጋገጥ እንዲተጋ ጠይቀዋል።

የሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ መርጋ ምትኬ በበኩላቸው በዞኑ የነበሩ አንዳንድ አመራሮች የተጣለባቸውን ኃላፊነት በመዘንጋት የግል ጥቅማቸውን በማስቀደም ሕዝቡን መጉዳታቸውን ተናግረዋል፡፡

"በዚህም የፀጥታ ችግር በሕዝቡ ልማት ላይ አሉታዊ ተጽህኖ ተፈጥሮ ነበር" ያሉት አቶ መርጋ "አሁን የተገኘውን አንፃራዊ ሠላም በመጠቀም ሕዝቡ ከለውጡ አመራር ጋር በመሆን ሰላሙን ወደ ነበረበት በመመለስ ልማቱን ማስቀጠል አለበት"ብለዋል።

አዲስ የተመደበው የለውጥ አመራርም ሕዝቡ የልማትና የሰላም ተጠቃሚ እንዲሆን በግልጽነትና በቅንነት በማገልገል የተጣለበትን ሃላፊነት መወጣት እንዳለበት ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም