ምክር ቤቱ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነት ማጽደቂያ አዋጅን አፀደቀ

112

አዲስ አበባ  መጋቢት 12/2011 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነት ማጽደቂያ አዋጅን አፀደቀ።

ምክር ቤቱ ባለፈው ጥር 30 ቀን 2011 ዓ.ም. ባካሄደው 24ኛ መደበኛ ጉባኤ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነት መቋቋሚያ አዋጅ  ከተመለከተ በኋላ ረቂቅ አዋጁን ለዝርዝር እይታ በዋናነት ለውጪ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እንዲሁም በተባባሪነት ለንግድና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቶት ነበር።

በመሆኑም ቋሚ ኮሚቴዎቹ በረቂቅ አዋጁ ምርመራ ሂደት የተከወኑ ተግባራትን፣ በአስረጂነት የተገኙ ኃላፊዎችን እና በምርመራ ሂደት የተለዩ ጭብጦችን ለምክር ቤቱ አቅርበው ረቂቅ አዋጁ እንዲፀድቅ ጠይቀዋል።

ምክር ቤቱም ቋሚ ኮሚቴዎቹ ያቀረቡትን የውሳኔ ሀሳብ መርምሮ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነት ማጽደቂያ አዋጅን በሙሉ ድምጽ አጽድቆታል።

አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጠናው 'ያስፈልገናል' በሚል 52 የአፍሪካ ህብረት አባል አገሮች ፈርመዋል።

የአፍሪካ ህብረት ይህንን ለማስፈጸም ሰፊ ስራ እያከናወነ የሚገኝ ሲሆን ወደተግባር ለማስገባት እንዲቻል ከህብረቱ አባላት ውስጥ ቢያንስ 22 አገሮች የስምምነት ማጽደቂያ አዋጁን በየምክር ቤቶቻቸው ማጸደቅ አስፈላጊ በመሆኑ አዋጁን እያጸደቁ ይገኛሉ።

እስካሁን ድረስ ኢትዮጵያን ጨምሮ 20 አገሮች ያጸደቁት ሲሆን ወደተግባር ለመግባት የሁለት የህብረቱ አባል አገሮች በምክር ቤት ማጸደቃቸው እየተጠበቀ ነው።

ነጻ የንግድ ቀጠናው ወደስራ ሲገባ ከአንድ ቢሊዮን ሰዎች የገበያ ተደራሽ ከመሆን ባለፈ ከ3 ነጥብ 4 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ የሆነ የአገር ውስጥ ምርት ግብይት የሚካሄድበት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

ነጻ የንግድ ቀጣናው ወደተግባር ሲገባ አህጉራዊ የንግድ ውድድርን በማጠናከር፣ የስራ ዕድልን በማስፋት፣ ምርታማነትን በማሳደግ፣ አህጉራዊ የንግድ መዳረሻን በማስፋፋት ረገድ ጠቀሜታ ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም