የአዲስ አበባ ከተማ የመሰረተ ልማት ቅንጅት የግንባታ ፈቃድ ባለስልጣን ‘ግንባታዎችን ለመቆጣጠር በቂ የሰው ሃይል የለኝም’ አለ

234

አዲስ አበባ መጋቢት 12/2011 በአዲስ አበባ ከተማ የሚከናወኑ ግንባታዎችን ለመቆጣጠር በቂ የሰው ሃይል እንደሌለው የአስተዳደሩ መሰረተ ልማት ቅንጅት የግንባታ ፈቃድ ባለስልጣን ገለጸ።

እየተገነቡ ባሉ የህንጻ  ግንባታዎች ላይ ያለው የቁጥጥር ማነስና የጥራት ጉደለት ለሰው ህይወት መጥፋት መንስኤ እየሆነ መጥቷል።

በከተማው በርካታ የህንጻ ግንባታዎች  ቢካሄዱም የግንባታውን ያህል ቁጥጥር እየተደረገ እንዳልሆነ የግንባታ ባለሙያና የተቋማት ሃላፊዎች ይናገራሉ።

በከተማው በቅርቡ ህንጻ ላይ እየተገጠመ ያለ የአሳንሰር (ሊፍት) መወጣጫ ተደርምሶ የሁለት ሰዎች ህይወት ሲጠፋ ሌሎችም ለአካል ጉዳት መዳረጋቸው ይታወሳል።

የአዲስ አበባ እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ኤጀንሲ እንደሚለው፤ የግንባታ ጥራት ችግር፣ የቁጥጥር ማነስና ቸልተኝነት የአደጋ ተጋላጭነት መንስኤ መሆናቸውን ይገልጻል።

የኮንስትራከሽን ባለሙያ የሆኑት ኢንጂነር ዮናስ እጅጉ እንደሚሉት፤ በአገሪቱ በርካታ ግንባታዎች ቢካሄዱም የጥራት መጓደልና የግብዓቶች ደረጃቸውን አለመጠበቅ በዘርፉ በስፋት የሚስተዋሉ ችግሮች ናቸው።

በተጨማሪ የግንባታ ባለሙያዎችም አቅም ማነስ፣ የኮንትራክተሮችና አማካሪዎች ቸልተኝነት፣ ጥራት የሌላቸው የግንባታ ዕቃዎችን መጠቀምና ፈቃድ የሰጠው አካል ተከታትሎ የግንባታውን ጥራት ያለመቆጣጠሩ የጥራት ችግሩ ምንጭ መሆናቸውን አመልክተዋል።

የግንባታ ጥራትን መቆጣጠር ያለበት የመንግስት አካል ቢሮ ተቀምጦ በሚሰራው ስራ የሚፈለገውን ጥራት ማምጣት እንደማይቻል ገልጸው ኮንትራክተሮች፣ አማካሪዎችና የመንግስት አካል በሚሰሩት የጋራ ስራ የተሻለ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ጠቁመዋል።

በተለይም መንግስት ለጉዳዩ በቂ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት ኢንጂነር ዮናስ ተናግረዋል።

በግንባታ ወቅት የሚደርሰውን አደጋ ለመከላከልም ባለሙያዎች የአደጋ መከላከያ የመጠቀም ልምዳቸውን እንዲያሳድጉ ኮንትራክተሮችና አማካሪዎች በቂ ስልጠና መስጠት እንዳለባቸው የህንጻ ባለቤት የሆኑት አቶ ያሬድ ጌታቸው ተናግረዋል።

”ኮንትራክተሮችና አማካሪዎች የተሰጣቸው በቅንናት በትጋት በመወጣት ሰዎችን ከአደጋ የመታደግ ስራቸውን መወጣት ይገባል” ብለዋል።

እንደ አቶ ጌታቸው ገለጻ፤ የግንባታ ባለሙያዎች የሚቀርብላቸውን የስራ ላይ ደህነንት መጠበቂያዎችን ‘ይሞቀናል፣ ይከብደናል’ በሚል ምክንያት እንደማይገለገሉበት ጠቁመዋል።

የግንባታ ጥራትን የሚቆጣጠረው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሰረተ ልማት ቅንጅት የግንባታ ፈቃድ ባለስልጣን በቂ የሆነ የሰው ሃይል የሌለው በመሆኑ በተገቢው መጠን ቁጥጥር እያደረገ እንዳልሆነ ይገልጻል።

የባለስልጣኑ የግንባታ ክትትልና ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ ሙሉጌታ ሊግዲእንደሚገልጹት፤ በከተማው የሚካሄደው ግንባታና ተቋሙ ያለው የሰው ሃይል ተመጣጣኝ አይደለም።

ደረጃውን ባልጠበቀ የግንባታ ግብዓት የሚከናወን ግንባታ በጥራት ጉድለት የተነሳ እየተደረመሰና እየፈረሰ ጉዳት እያስከተለ መሆኑን ገልጸዋል።

ከአምስት ወለል በላይ ያሉ ህንጻዎችን ላይ ቁጥጥር የሚያደርገው ባለስልጣኑ ተገቢውን ቁጥጥር ለማድረግ የሚያስችለውን መዋቅር ለመፍጠር ዝግጅት እያደረገ እንደሚገኝ አቶ ሙሉጌታ አስረድተዋል።

ባለስልጣኑ ለተለያዩ ተቋማት የግንባታ ፈቃድ የሚሰጥ በመሆኑም የሰው ሃይሉ ላይ ጫና እንዳለበት አመልክተዋል።

የቅጣቱ እርከን አዋጁ አስተማሪ ባለመሆኑ የዲዛይን ለውጥና ሌሎች የግንባታ ችግሮችን ፈጽመው የሚቀጡ ባለሃብቶች እየተበራከቱ መሆኑን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

”የቅጣቱ አስተማሪ አለመሆንና የግንባታ ጥራት መበራከት አደጋዎች እንዲበራከቱና ህገ-ወጥነት እንዲስፋፋ አደርጓል” ብለዋል።

በተጨማሪ የተቋማት የቅንጅት ስራ አለመኖርና የግንባታ ባለሙያዎች የስራ ላይ ደህነነት መጠበቂያ በአግባባ አለመጠቀም ችግሩን እያባባሰ እንደሆነም ገልጸዋል።

ችግሩን ለመፍታት ባለሙያዎች፣ የህንጻ ባለቤቶች፣ ኮንትራክተሮችና አማካሪዎች በቅንነት አገራቸውን ማገልገልና ዜጎችን ከሞት መታደግ እንዳለባቸው አቶ ሙሉጌታ ተናግረዋል።

በግንባታ ላይ በሚፈጠር ችግር ባለፉት ሶስት ዓመታት 17 ሰዎች ለሞት 58 ሰዎች ለአካል ጉዳት የተዳረጉ ሲሆን በተለይ በዚህ ዓመት አደጋው ጨምሯል።