በትግራይ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ስምንተኛ ዓመት በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል

350

አክሱም መጋቢት 12/2011 የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መሰረት ድንጋይ የተጣለበት ስምንተኛ ዓመት በክልል ደረጃ በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበር የትግራይ ክልል የህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ገለጸ።

ጽሕፈት ቤቱ ግድቡ አሁን ያለበት ደረጃና ወቅታዊ የመረጃ ልውውጦች ላይ ያጋጠሙ ክፍተቶችን ለማስተካከል በክልሉ እንደሚሰራም አስታውቋል።

የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ገብረሚካኤል መለስ ለኢዜአ እንደገለጹት የግድቡ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠበት ስምንተኛ ዓመት ሲከበር በአንዳንድ መገናኛ ብዙሃን ስህተት ህዝቡ ላይ የተፈጠረውን ጥርጣሬ ግልጽ የማድረግ ስራ ይሰራል።

በዚህም ህዝቡ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦችን ያስተሳሰረውን ታላቁ የህዳሴ ግድብ አሁን ያለበትን የግንባታ ደረጃ ግልጽ መረጃ እንዲያገኝ እንደሚደረግ አስረድተዋል።

በታላቁ የህዳሴ ግድብ አማካኝነት የተጀመረውን የቁጠባ ባህል ማዳበር የበዓሉ አንድ አካል መሆኑንም ገልጸዋል።

“በክልሉ ፖሊስ ማርሽ ባንድ የታጀበ የህዳሴ ትርኢት በመቀሌ ከተማ በመዘዋወር የህዝቡን እምነት የመመለስና የማነቃቃት ስራ ከሁለት ቀናት በፊት ከመካሄዱ በተጨማሪ መጋቢት 15 ቀን ደግሞ ክልል አቀፍ የፓናል ውይይት ይካሄዳል” ብለዋል፡፡

ግልጽነትን በማስፈን ቁጠባን ማበረታታት እንደሚገባ የሚያመለክት መልዕክት በሚኖረው የፓናል ውይይት ላይም በርካታ ሰዎች እንደሚሳተፉ ተናግረዋል።

ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረ ጀምሮ የክልሉ ህዝብ ቦንድ ከመግዛት በተጨማሪ በስጦታና ሌሎች ለግድቡ ገንዘብ ማሰባሰቢያ በተዘጋጁ ሁነቶች  ከፍተኛ ተሳትፎ ማበርከቱን ገልጸዋል፡፡

“አንዳንድ መገናኛ ብዙሀንም የተቆራረጠና የተሳሳተ መልእክት በማስተላለፍ በህዝቡ ዘንድ የፈጠሩትን ጥርጣሬና ብዥታም በመፍታት ህዝቡ ዳግም እንዲነሳሳ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል” ብለዋል፡፡

ታላቁ የህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያንን ያስተሳሰረና ህዝቡ በፍላጎቱ ገንዘቡን ማዋጣቱን ትልቅ ተስፋ የጣለበት መሆኑን የገለጹት ደግሞ በመቀሌ የፕላኔት ሆቴል ስራ አስክያጅ አቶ ሙሉ ሓዱሽ ናቸው።

ስራ አስክያጁ እንዳሉት ሆቴሉና የሆቴሉ ሰራተኞች በሙሉ ፍላጎትና በፍቃደኝነት በመመስረት ከ250ሺህ ብር በላይ የቦንድ ግዢ መፈጸማቸውን ተናግረዋል፡፡

አሁን የተፈጠረውን መቀዛቀዝ በመፍታት ህዝባዊ ተሳትፎውን አጠናክሮ የማጠናቀቅ ግዴታ እንዳለበት ገልጸው ግድቡ ከስራ አጥነት ተያይዞ እየተፈጠረ ያለውን ችግር ያስቀራል የሚል እምነት እንዳላቸው አቶ ሙሉ ተናግረዋል፡፡

“ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ በአገሪቱ ኢኮኖሚና በግለሰቦች ገቢ ላይ አወንታዊ ሚና ያለው በመሆኑ ኢትዮጵያውያን እንዳጋመስነው ለማጠናቀቅ መነሳሳት አለብን” ብለዋል፡፡