ዋልያ ቢራ ከእግር ኳስ ብሔራዊ ቡድኑ ጋር የ56 ሚሊዮን ብር የውል ስምምነት ተፈራረመ

96

አዲስ አበባ መጋቢት 12/2011 ዋልያ ቢራ ለቀጣይ አራት ዓመታት የሚቆይ የ56  ሚሊዮን ብር የስፖንሰር ሺፕ ስምምነት ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን ጋር ተፈራረመ።

የውል ስምምነቱም ትናንት ምሽት በካፒታል ሆቴል ነው የተፈረመው።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የውል ስምምነቱ ከያዝነው ዓመት ጥር ጀምሮ እስከ አራት ዓመታት ድረስ የሚቆይ ነው።

በዚህ ዓመታት ውስጥም አክሲዮን ማህበሩ ለፌደሬሽኑ 56 ሚሊዮን ብር የሚከፍል ሲሆን ክፍያውም በየሶስት ወሩ እንደሆነ ገልጸዋል።

ዋልያ ቢራ ይህን ስምምነት ያደረገው ከሌላው ጊዜ በተለየ መልኩ በሀገሪቱ የአልኮል መጠጦች በሬዲዮና በቴሌዥን ለማስተዋወቅ የሚከለክል አዋጅ በወጣበት ዓመት መሆኑ ነው።

ባሳለፍነው ጥር ወር  የምግብ፣ መድኃኒትና ጤና ክብካቤና ቁጥጥር ባለስልጣን ያፀደቀው አዋጅ በቀጣይ ዝርዝር ጉዳዮች ይፋ ሲሆኑ ተቋማቱ ምርታቸውን  ለማስተዋወቅ ሰፊ እድል የማይፈጥር ቢሆንም እንኳ ውሉ እንደማይፈርስ ነው የገለጹት።

አቶ ኢሳያስ አክለውም የአልኮል መጠጦችን ለማስተዋወቅ ሰፊ አማራጭ በማያግኝበት በዚህ ወቅት ዋልያ ቢራ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጎን መሆኑ እግር ኳሱን ለመደገፍ አጋርነቱን በማሳየቱ ታላቅ ምስጋና አለን ብለዋል።

የሃይኒከን ኢትዮጵያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሚስተር ዪጂን ዩባሊጀሮ ሃይኒከን ''ከዋልያዎቹና ከሉሲዎቹ ብሄራዊ ቡድን ጋር በአጋርነት ሲሰራ ትልቅ ኩራት ይሰማዋል'' ብለዋል።

ሃይኒከን ከህዝብ ጋር አብሮ የማደግ ፍላጎት ያለው ኩባንያ  በመሆኑም ከኢትዮጵያን ጋርም አጋሪነቱ ሰፊ ነው ብለዋል።

የሃይኒከን ምርት የሆነው ዋልያ ቢራ አክሲዮን ማህበር ባለፉት አራት ዓመታትም ከወንዶቹ እግር ኳስ  ብሄራዊ ቡድን ጋር ለአራት ዓመታት 56 ሚሊዮን ብር ስፖንሰር እንደነበር ይታዋሳል።

በዚህ ዓመትም በተመሳሳይ የገንዘብ መጠን እንደገና ውሉን ሲያድስ ከወንዶች በተጨማሪ የሴቶቹንም ብሄራዊ ቡድን በቦርሳዎች ላይና ሌሎች አልባሳት ላይ በመጠቀም ምርቱን ማስተዋወቅ ይችላል ተብሏል።

ከዚህ በተመጨማሪ በቢል ቦርድ የአልኮል መጠጥን ማስተዋወቅ የሚፈቀድ ከሆነም ይህን እንዲያደርግ ፌዴሬሽኑ እድል እንደሚሰጠው ተግልጿል።

የአሁኑ ክፍያ ባለፈው አራት ዓመት ዋልያ ቢራ ከከፈለው እኩል የገንዘብ መጠን ያለው ሲሆን በዚህ ዓመት ከወንዶቹ  በተጨማሪ ሉሲዎችንም በመጠቀም ምርቱን እንዲያስተዋውቅ ተጨማሪ እድል ተስጥቶታል።

ይህ ተጨማሪ እድል የተሰጠውም በሀገሪቷ የአልኮል መጠጥ አስመልክቶ የፀደቀው አዋጅ  እንደበፊቱ ምርታቸውን ለማስተዋወቅ ሰፊ እድል የማይሰጥ በመሆኑ ነው።

ሃይኒከን ከሚያምርታቸው የአልኮል መጠጦች በተጨማሪ ከአልኮል ነጻ የሆነው የሶፊ ማልት ምርቱ ደግሞ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን  ስፖንሰር እንደሆነ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም