የብሪታንያ ብሔራዊ ጦር ቤተ-መዘክር የአጼ ቴዎድሮስ ሽሩባ ለኢትዮጵያ መንግስት አስረከበ

104

አዲስ አበባ መጋቢት 12/2011 የብሪታንያ ብሔራዊ ጦር ቤተ-መዘክር የአጼ ቴዎድሮስ ሽሩባ (ቁንዳላ) ለኢትዮጵያ መንግስት አስረከበ።

በብሪቲሽ ብሄራዊ ሙዚየም የሚገኙ ጽላቶች እንዲመለሱም የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጠይቋል።

የአጼ ቴዎድሮስ መለያ የሆነው ሽሩባ ፀጉራቸውን ጨምሮ ሌሎች የአገሪቱ ቅርሶችን ለማስመለስ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው የተመራ ልዑካን ቡድን ቅርሶቹ ወደሚገኙበት እንግሊዝ አገር መጋቢት 9 ቀን 2011 ዓ.ም ማቅናቱ ይታወሳል።

የአጼ ቴዎድሮስ ሽሩባ ርክክብ ሥነ-ስርዓት ትናንት ማምሻውን ለንደን በሚገኘው የብሪታንያ ብሔራዊ ጦር ቤተ-መዘክር እንደተካሄደ ብሪታንያ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በድረ-ገጹ ይፋ አስፍሯል።

ይህን ተከትሎም የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው ትናንት በቤተ-መዘክሩ በተካሄደ ስነ ስርአት የአጼ ቴዎድሮስን ሽሩባ ከብሪታንያ ብሔራዊ ጦር ቤተ-መዘክር ዋና ዳይሬክተር ሚስተር ጀስቲን ማሲጄውስኪ ተረክበዋል።

እ.አ.አ በ1868 መቅደላ ላይ አጼ-ቴዎድሮስ 'ለእንግሊዝ ወታደሮች እጅ አልሰጥም' ብለው ራሳቸውን እንደሰዉ የታሪክ ድርሳናት ይገልፃሉ።

የአፄውን በዚህ መልኩ ማለፍ ተከትሎም በርካታ የኢትዮጵያ ቅርሶች በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ ከአገር ሸሽተው በተለያዩ የአውሮፓ አገሮች እንደሚገኙ ይታወቃል።

ባለፈው የፈረንጆች አመት ለንደን የሚገኘው የብሪታንያ ብሔራዊ ጦር ቤተ-መዘክር በድረ-ገጹ ላይ የአጼውን ፀጉር ምስል ማሰራጨቱ፤ በአውደ-ርእይ ላይም ለህዝብ ማቅረቡ ብዙዎችን አስቆጥቶ እንደነበርም ይታወሳል።

ይህንን ተከትሎም የኢትዮጵያ መንግስት ቅርሱ ወደአገር ቤት እንዲመለስ ጥረት መጀመሩንና ሚኒስቴሩ በኢንግሊዝ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር በመሆን የአፄውን ፀጉር ለማስመለስ በቀረበው ጥያቄ መሰረት ብሪታኒያ ከ150 ዓመት በፊት የተወሰደውን ይህንን ሽሩባ ፀጉር ለመመለስ ፍቃደኛ መሆናቸውም ይታወቃል።

የአጼ ቴዎድሮስ ሽሩባ ጸጉር ወደ አገሩ ለመመለስ የተደረገው ርክክብ ትልቅ ታሪካዊ ኩነት እንደሆነ ኤምባሲው ገልጿል።

ሌሎች ቅርሶችም በሚመለሱበት መንገድ ላይ የልዑካን ቡድኑ ከተለያዩ ተቋማት ጋር እየመከረ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።

የልዑካን ቡድኑ ትናንት በለንደን የብሪቲሽ ብሄራዊ ሙዚየም ጉብኝት ያደረገ ሲሆን በሙዚየሙ የሚገኙ ጽላቶች እንዲመለሱ መጠየቁን ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የባህልና ቱሪም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው ውይይት ያደረጉ ሲሆን ሙዚየሙ በአለም ስመ ጥርና የተደራጀ መሆኑን በመጠቆም በኢትዮጵያ የሙዚየም ግንባታና አደረጃጀት ላይ አብሮ መስራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

የሙዚየሙ ሃላፊዎችም ኢትዮጵያን መጎብኘት እንደሚፈልጉና አብረው ይሰሩ እንደነበር በመግለጽ ወደፊትም በጋራ መሥራት እንደሚፈልጉና ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡም የመግባቢያ ሰነድ እንደሚፈራረሙ ተገልጿል።

ሚኒስትሯ በሙዚየሙ የሚገኙ ታቦታት ለኢትዮጵያውያን ኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ልዩ ክብርና ቦታ ያላቸው ከፈጣሪያቸው ጋር የሚገናኙባቸው ህያው በመሆናቸው ወደ ትክክለኛ ቦታቸው እንዲመለሱ ጠይቀዋል።

የሙዚየሙ ሀላፊዎች ሀሳቡን እንደሚጋሩትና የህግ ጉዳይ ሆኖ መወሰን ባይችሉም በሚቀጥለው ሃምሌ ወር 2011 ላይ በሚኖራቸው ስብስባ ለአገሪቱ ሙዚየም ባለአደራ ቦርድ አቅርበው ምላሽ እንደሚሰጡ ገልጸዋል።

በመቀጠልም በሙዚየሙ ጉብኝት የተደረገ ሲሆን በርካታ ቅርሶች እንደሚገኙ መመልከት መቻሉን ሚኒስቴሩ ገልጿል።

በሌላ በኩል የልዑካን ቡድኑ ከትናንት በስቲያ ለንደን በሚገኘው የብሪቲሽ ቤተ-መዘክር ጉብኝት ያደረገ ሲሆን ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳው ከብሪታንያ ቤተ-መዘክር ጋር የመግባቢያ ሰነድ ፈርመዋል።

የመግባቢያ ሰነዱ ብሪታንያ እና ኢትዮጵያ በጥናታዊ ጉዳዮች እና በአቅም ግንባታ ዙሪያና በጽሁፍ ሀብቶች እንክብካቤ ዲጅታላይዝ በማድረግ በትብብር ለመሥራት ያስችላቸዋል ተብሏል።

በጉብኝቱ ወቅት የቤተ-መዘክሩ ዋና ዋና ክፍሎች የተጎበኙ ሲሆን በዋናነት ከመቅደላ የተወሰዱ ብርቅዬና ድንቅ ጥበብ ያረፈባቸውን የጽሁፍ ቅርሶች እንዲሁም ቅርሶቹ የሚጠግኑበትንና በዲጂታል ቴክኖሎጂ በመጠቀም የሚጠብቁበትን መንገድ ልዑካን ቡድኑ ተመልክተዋል።

የቤተ-መዘክሩ አመራሮች በኢትዮጵያ በመገኘት ዲጅታላይዝ የተደረጉ መፃህፍትን ለማበርከትና የቴክኖሎጂ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

ሚኒስትሯ በጉብኝቱ ወቅት ባደረጉት ውይይት ሁለቱ አካላት በቀጣይ በጋራ ለመስራት መግባባታቸውን አድንቀውና አመስግነው ''በብሪቲሽ ቤተመፃህፍት የሚገኙ የፅሁፍ ሀብቶቻችን ከቅርስነትና ከቱሪዝም ሀብትነት በላይ የእውቀትና የእድገት መሰረቶችም ናቸው'' ብለዋል።

አንድ አገር የተሟላ እድገት ለማምጣት የእውቀት ካፒታል ስለሚያስፈልገው ሀብቶቹ ለኢትዮጵያውያን የሚያስፈልጉ በመሆናቸው ሊመለሱ እንደሚገባ በመግለጽ በኢትዮጵያ ህዝብ ስም ጥያቄያቸውን አቅርበዋል።

በእንግሊዝ የሚገኘው የአጼ ቴዎድሮስ ልጅ የልዑል አለማየሁ ቴዎድሮስ  አፅም ለኢትዮጵያ ተመልሶ እንዲሰጥ እየተደረገ ባለው ጥረት ላይ ልዑካን ቡድኑ ውይይት ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።

የልኡሉ አፅም የዘረ-መል (ዲኤንኤ) ምርመራ ከአባትየው ፀጉር በመውሰድ በማካሄድ የአፅሙን ማንነት የማረጋገጡ ተግባር በሂደት ላይ መሆኑም ተገልጿል።

በባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው የተመራው ልዑካን ቡድን ቅዳሜ መጋቢት 14 ቀን 2011 ዓ.ም ረፋድ ላይ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመለስም ሚኒስቴሩ አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ቅርሶች በአብዛኛው በእንግሊዝ፣ በጀርመንና በጣልያን አገር የሚገኙ ሲሆን ወደ አገር ቤት ለማስመለስ በአገሮቹ በሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች በኩል ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ እንደሆነም ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም