በጋምቤላ ክልል ሕገ ወጥ ንግድ እንቅስቃሴን ለመቀነስ ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መሥራት እንዳለባቸው ተጠቆመ

292

ጋምቤላ መጋቢት 11/2011በጋምቤላ ክልል እየተስፋፋ ያለውን ገቢና ወጪ ሕገ ወጥ  ንግድ እንቅስቃሴን ለመቀነስ ባለድርሻ አካላት በቅንጅት እንዲሰሩ ተጠየቀ።

በሕገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴ መከላከያ መንገዶች ላይ ባለድርሻ አካላት ትናንት በጋምቤላ ከተማ ተወያይተዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት የመቆጣጠሪያ ኬላዎችና ቅንጅታዊ አሰራር ባለመጠናከራቸው ሕገ ወጥ ንግድ እየተስፋፋ መጥቷል።

ከተሳታፊዎቹ መካከል አቶ ቸኮል በለጠ በሰጡት አስተያየት በክልሉ ጠረፋማ አካባቢዎች የመቆጣጠሪያ ኬላዎች የሚፈለግባቸውን ተግባር እያከናወኑ አለመሆናቸውን አስረድተዋል።

በተለይም መንግሥት ለሕዝብ በድጎማ የሚያመጣቸው የስኳር፣ የዘይት፣የዳቦ ዱቄትን ጨምሮ የፍጆታ ዕቃዎች በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ጎረቤት አገር እየወጡ ነው ብለዋል።

በጎረቤት አገሮች በኩል ድንበር አቋርጦ እየገቡ ያሉት ሕገ- ወጥ የጦር መሣሪያዎች ፣መድኃኒትና ምግብ ነክ ዕቃዎች አመራሩ ሕዝቡን አሳትፎ ያለመስራቱ ችግር ነው ያሉት ደግሞ ሌላው ተሳታፊ አቶ ዓለማየሁ ክብረት ናቸው።

ስለሆነም በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች የኅብረተሰቡን ተሳትፎና አደረጃጀት በማጠናከር ሕገ ወጥ ንግድ መከላከል እንዳለባቸው አመልክተዋል።

ምክትል ኢንስፔክተር ጋትዊች ኩክ እንደሚሉት በተለይም በመግቢያና መውጫ በሮች ያሉት የጉምሩክ የመቆጣጠሪያ ኬላዎች አለመጠናከር ለችግሩ ዋነኛ መንስዔ ናቸው ብለዋል።

”ሕገ ወጥ ጦር መሣሪያዎች በምን መልኩ ከደቡብ ሱዳን ወደ ክልሉ እየገቡ እንደሆነ ለአመራሩም ሆነ ለኅብረተሰቡ የተሰወረ ነገር አይደለም” ያሉት ደግሞ በፌዴራል ፖሊስ የምዕራብ ዲቪዥን አዛዥ ኮማንደር ማሙዬ አባተ ናቸው።

ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያዎች ዝውውር ለመግታት ከክልል እስክ ወረዳ ያለው አመራር በቁርጠኝነትና በቅንጅት ካልሰራ ከችግሩ መውጣት እንደማይቻልም ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን የደንቦኞች አገልግሎትዳይሬክተር አቶ መንግስቱ ተፈራ ኮሚሽኑ በክልሉ ሶስት ዋና በሮች ላይ የመቆጣጠሪያ ኬላዎችን የማቋቋምና የማደረጀት ሥራ እያከናወነ ነው ብለዋል።

በቀጣይም የክልሉ መንግሥት የሕገ ወጥ ንግድ መግቢያና መውጫ በሮች ናቸው ብሎ ለይቶ በሚያቀርባቸው ቦታዎች ላይ ተጨማሪ የመቆጣጠሪያ ኬላዎችን ለመክፈት ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ እየተበራከተ የመጣውን እንቅስቃሴ የሚገታው ከክልል አስከ ቀበሌ ሕዝቡን ያሳተፈ የተጠናከረ አደረጃጀት ለመፍጠር በትኩረት እንዲሰራ ጠይቀዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በመድረኩ ላይ እንደተናገሩት የክልሉ መንግሥት የክልሉን ብሎም የአገርን ኢኮኖሚ የሚጎዳውን ሕገ ወጥ ንግድ ለመከላከል በየደረጃው የተጠናከረ አደረጃጀት በመፍጠር ችግሩን ለመግታት በትኩረት ይሰራል።

በተለይም ክልሉ ጠረፋማ ከመሆኑ አኳያና ለሕገ ወጥ ንግድ ባለው ተጋላጭነት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ችግሩን ለመግታት እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

በጋምቤላ ከተማ በተካሄደው በዚህ የምክክር መድረክ ላይ በየደረጃው ያለው አመራሮችና የፌዴራልና የክልሉ የጸጥታ አካላት ተሳታፊዎች ነበሩ።