በደጀን ዙሪያ ወረዳ በ8 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ወጪ ሲሚንቶ ፋብሪካ ግንባታ ተጀመረ

54

ደብረ ማርቆስ  መጋቢት 11/2011 በምሥራቅ ጎጃም ዞን ደጀን ዙሪያ ወረዳ በ8 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር የሲሚንቶ ፋብሪካ ግንባታ ዛሬ ተጀመረ፡፡

ፋብሪካው ለ1ሺህ 500 ዜጎች ሥራ ሲፈጥር፣በዓመት ሁለት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ኩንታል ሲሚንቶ ያመርታል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር አምባቸው መኮንን በግንባታው ማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓት ላይ ለፋብሪካው ግንባታ ከቦታቸው የተነሱ አርሶ አደሮች ከግንባታው እስከ ምርቱ ሂደት በማሳተፍ  ተጠቃሚዎች ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በክልሉ ተጨማሪ ፋብሪካዎች እንዲገነቡ ጥረቱ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።

መንግሥት ኢንቨስትመንትን በማስፋፋት የክልሉን ሕዝብ ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል፡፡

በኢንቨስትመንት ዘርፍ የሚሰማሩ ባለሀብቶችን በመደገፍ ፈጣን አገልግሎት እንዲያገኙ ለማድረግም እየተንቀሳቀሰ ነው ብለዋል።

በአማራ ክልል በምክትል ርእሰ መስተዳደር ማዕረግ የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ  የፋብሪካው የቦርድ ሰብሳቢ አቶ መላኩ አለበል በበኩላቸው ፋብሪካውን በታለመለት ጊዜ ለማጠናቀቅ እገዛ እንደሚደረግለት  አመልክተዋል።

ፋብሪካውን የሚገነቡት የቻይናና የዴንማርክ  ኩባንያዎች ከ130 ዓመታት የካበተ ልምድ ያላቸው መሆናቸውንም አስረድተዋል።

ግንባታውንም በጥራትና በታማኝነት እንዲሁም በኃላፊነት እንዲያከናወን አቶ መላኩ አሳስበዋል።

የዓባይ ሲሚንቶ ፋብሪካ ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር አስራት ኪዳኑ በበኩላቸው የፋብሪካውን ግንባታ 24 ወራት ጊዜ ውስጥ አጠናቆ ለማስረከብ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

ፋብሪካው ለ1ሺህ 500 በላይ ዜጎች ሥራ እንደሚፈጥርም ገልጸዋል፡፡

ፋብሪካው የማምረት ሥራ ሲጀምርም በዓመት ሁለት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ኩንታል ሲሚንቶ እንደሚያመርት ሥራ አስኪያጁ አስታውቀዋል።

በሥነ ሥርዓቱ ላይ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮችና የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

በኢትዮጵያ 10 የሚደርሱ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች እንደሚገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም