ምክር ቤቱ በጥራት ላይ የሚሰሩ ተቋማትን ማጠናከር ያስፈልጋል አለ

59

አዲስ አበባ መጋቢት 11/2011 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ኢትዮጵያ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ እንድትሆን ጥራትን የሚያረጋግጡ ተቋማት መጠናከር እንዳለባቸው አሳሰበ።

በምክር ቤቱ የንግድና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ የደረጃዎች ኤጀንሲንና የተስማሚነትና ምዘና ድርጅትን የስራ እንቅስቃሴ ምልከታ አድርጓል።

የቋሚ ኮሚቴ አባላት የተቋማቱን የለውጥ ስራና የስራ አካባቢ ተዘዋውረው በመጎብኘት ትኩረት መሰጠት ያለባቸው ጉዳዮች ላይ አስተያየት ሰጥተዋል። 

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ጌታቸው መለሰ የኢትዮጵያ የደረጃዎች ኤጀንሲ ከ12 ሺህ በላይ ደረጃዎች በወረቀት ላይ እንደሚገኙ በጉብኝታቸው መታዘባቸውን ተናግረዋል።

በመሆኑም በወረቀት የሚገኙ ደረጃዎችን ወደ ዲጅታል በመቀየር ለአሰራር አመች ማድረግና ከአደጋም መጠበቅ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በተመሳሳይ የተስማሚነትና ምዘና ድርጅት በሺዎች የሚቆጠር ገንዘብ የወጣባቸው ማሽኖች በመለዋወጫ እቃ እጥረት ምክንያት ያለ ስራ መቀመጣቸውን በጉብኝታቸው አረጋግጠዋል።

በላብራቶሪ ውስጥ መደረግ ካለባቸው ጥንቃቄዎች ጋር በተገናኘም ለሰራተኞችና ድርጅቱን ለሚጎበኙ ደንበኞች ተገቢው ጥንቃቄ እየተደረገ ባለመሆኑ ትኩረት መደረግ እንዳለበት አሳስበዋል።

በድርጅቱ ውስጥ የሚገኙ የተወሰኑ ላብራቶሪዎች ከደንበኞች ናሙና ባለመምጣቱ ወደ ስራ አለመግባታቸውንም ቋሚ ኮሚቴው በጉብኝቱ ወቅት ታዝቧል።

በተጨማሪም በኢትዮጵያ ተስማሚነትና ምዘና ድርጅት የእድሳት ዘመናቸው ያለፈ 6 ላብራቶሪዎች እንደሚገኙ በመግለጽ በፍጥነት እድሳት እንዲደረግ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ተስማሚነትና ምዘና ድርጅት ዋና ዳሬክተር አቶ ተሻለ በልሁ ስራ ያቆሙ ላብራቶሪዎች የመለዋወጫ ግዥ ለማድረግ የውጭ ምንዛሬ እጥረት በማጋጠሙ መሆኑን ምላሽ ሰጥተዋል።

በአሁኑ ወቅትም ችግሩን ለመፍታትና የሰለጠነ ባለሙያ እንዲኖር ከሚመለከታቸው ጋር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

እንደዋና ዳሬክተሩ ገለጻ የላብራቶሪ እድሳቱን ለማድረግ ሂደቱ ረዥም በመሆኑ የተፈጠረ ችግር መሆኑን በማስረዳት እድሳቱን ለማድረግ በሂደት ላይ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ የደረጃዎች ኤጀንሲ ዋና ዳሬክተር አቶ እንዳለው መኮንን በሰጡት ምላሽም ደረጃዎችን ወደ ዲጅታል ለመቀየር አስፈላጊ እቃዎችን ለመግዛት እየተሰራ መሆኑን ገልጸው በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ እንደሚሆን አረጋግጠዋል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ጌታቸው መለሰ ኢትዮጵያ ከጥራት ጋር በተገናኘ በዓለም ገበያ እየገጠማት ያለውን ችግር ለመፍታት የውጭ ምንዛሬና ሌሎች ችግሮችን መንግስት በመፍታት ማጠናከር እንዳለበት አሳስበዋል።

ቋሚ ኮሚቴው ተቋማቱ የተሻለ የስራ አካባቢ ለመፍጠር እያደረጉ ያለውን ጥረት በጥንካሬ በማንሳት በለውጥ ውስጥ ካሉ ተቋማት መካከል መሆናቸውንም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም