በሲናና ወረዳ ትምህርት በመቋረጡ ቅሬታ ፈጥሯል

63

ጎባ መጋቢት 11/2011 የመማር ማስተማር ስራ ከሁለት ሳምንታት በላይ ተቋርጦባቸው ከትምህርት ገበታ በመስተጓጎላቸው ቅሬታ እንዳሳደረባቸው በባሌ ዞን ሲናና ወረዳ የተለያዩ ትምህርት ቤት ተማሪዎች  ገለጹ፡፡

የዞኑ ትምህርት ጽህፈት ቤት በበኩሉ መምህራን የስራ በማቆማቸው የተቋረጠውን የመማር ማስተማር ስራ ለማስጀመር ጥረት እየተደረገ  መሆኑን አስታውቋል ።

በወረዳው የሳምቢቱ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ኡስማን በከር ለኢዜአ እንዳለው በማያውቁት ምክንያት ከሁለት ሳምንታት በላይ  የመማር ማስተማር ስራው ተቋርጧል ።

"ትምህርቱ በመቋረጡ ለሀገር አቀፍ ፈተና በቂ ዝግጅት እንዳይኖረን የራሱን አሉታዊ ተፅእኖ ፈጥሮብናል" ብሏል ።

ላለፉት 15 ቀናት ከትምህርት ቤት መቅረታቸውን የተናገረችው  ደግሞ  የሳምብቱ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ሀምዚያ መሐመድ ናት፡፡

ትምህርቱ የተቋረጠው በመምህራን ምክንያት እንደሆነ ሲነገር መስማታቸውን ያመለከቱት  ተማሪዎቹ መምህራን  የመብት ጥያቄ ቢኖራቸው እንኳ እያስተማሩ መጠየቅ ይችሉ እንደነበር በማውሳት ቅሬታቸው ገልጸዋል ።

የሚመለከተው አካል አፋጣሽ መፍትሄ እንዲሰጣቸውም አመልክተዋል።

በወረዳው ሀሚዳ ቀበሌ የተማሪዎች ቤተሰቦች ኮሚቴ ተወካይ ሐጂ አህመድ ኡስማን  በበኩላቸው ኮሚቴው ትምህርት ስለተቋረጠበት ጉዳዩ እንደማያውቅ ተናግረዋል ።

"ትምህርት መቋረጡ በየትኛውም መስፈርት  አግባብ ባለመሆኑ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት እልባት ሊሰጥበት ይገባል" ብለዋል ።

በወረዳው የሳምቢቱ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር ፈይሳ ከተማ "መምህራን ተደራጅተን ላቀረብነው የቤት መስሪያ ቦታ ይሰጠን የመብት ጥያቄ ምላሽ በማጣታችን ስራ አቁመናል" ብለዋል ።

መምህሩ እንዳሉት ለአካባቢው መስተዳድር በተደጋጋሚ ላቀረቡት ጥያቄ  ምላሽ ሊሰጣቸው ባለመቻሉ እየሰሩ ከመጠበቅ ይልቅ ለጊዜው የማስተማር ስራቸውን ለማቆም መርጠዋል፡፡

የሮቤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ብርሃኑ ዲዲ ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ አስተዳደሩ የነዋሪዎችን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመፍታት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በተያዘው የበጀት ዓመት መምህራንን ጨምሮ በ20 ማህበራት ለተደራጁ  ከ1ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች የቤት መስሪያ ቦታ መሰጠቱን  ጠቅሰዋል ።

"አስተዳደሩ ባጋጠመው የመሬት አቅርቦት ችግር ከሲናና ወረዳ መምህራንና ሌሎች ነዋሪዎች ለቀረበለት ጥያቄ አፋጣኝ ምላሽ መስጠት አልቻለም" ብለዋል ።

እንደ ከንቲባው ገለጻ አስተዳደሩ ችግሩን ለመፍታት ጉዳዩ ከሚመለከተው ከክልሉ ከተማ ልማት ቢሮ ጋር እየተነጋገረ ነው።

የዞኑ ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጎሳ ግዛው በበኩላቸው በወረዳው የመማር ማስተማሩ ሂደት በመቋረጡ ተማሪዎች ላይ ስጋት መፍጠሩን ተናግረዋል ።

"መምህራን የመብት ጥያቄያቸውን በስራ ገበታ ላይ ሆነው መጠየው ሲችሉ ማስተማር በማቆማቸው በወረዳው ከሚገኙ  42 አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መካከል በ32ቱ የመማር ማስተማሩ ሂደት ተቋርጧል" ብለዋል ።

ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የዞኑ ሴክተር መስሪያ ቤቶችና የከተማ አስተዳደሮች ጋር ችግሩ በሚፈታበት አቅጣጫ ዙሪያ ውይይት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

"መንግስት የመምህራንን  የቤት ችግር ለመፍታት በሰጠው ትኩረት  የወረዳው መምህራን ጥያቄ አግባብነቱን ጠብቆ ይፈታል" ብለዋል ።

እንደ ኃላፊው ገለፃ በአጭር ጊዜ ውስጥ መደበኛ ስራቸውን በማይጀምሩ መምህራን ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ ይወሰዳል።

በባሌ ዞን በ875 የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከ490 ሺህ በላይ ተማሪዎች የዘመኑን ትምህርት  በመከታተል ላይ እንደሚገኙ ታውቋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም