ድርጅቱ በ17 ሚሊዮን ብር ወጪ ያስገነባቸው አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተመረቁ

334

አምቦ መጋቢት 11/2011 በሰዎች ለሰዎች ድርጅት በ17 ሚሊዮን ብር ወጪ በምዕራብ ሸዋ ዞን ግንደበረት ወረዳ የተገነቡ ሶስት የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ዛሬ ለአገልግሎት በቁ።

ለትምህርት ቤቶቹ ጥበቃና እንክብካቤ እንደሚያደርጉላቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል።

የግንደበረት ወረዳ ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ምኞት ተስፋዬ በምረቃው ሥነ ሥርዓት ላይ እንዳሉት ትምህርት ቤቶቹ 1 ሺህ 800 ተማሪዎችን ያስተናግዳሉ።

ካቺሲና ቂልጡ ሰንበታ በተባሉ የገጠር ቀበሌዎች የተገነቡት ትምህርት ቤቶች 36 የመማሪያ ክፍሎች አሏቸው።የመማሪያ ቁሳቁስ ተሟልቶላቸዋል።

ትምህርት ቤቶቹ ሕጻናት ከአካባቢያቸው ሳይርቁ  እንዲማሩ ከማስቻል ባለፈ፤ የተማሪዎች የትምህርት ማቋረጥ መጠንን እንደሚቀንስ ኃላፊው ተናግረዋል።

በተጨማሪም ለትምህርት ጥራትና ተደራሽነት አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ አመልክተዋል።

የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ አብዲሳ ሌንጅሳ የአካባቢዎቹ ነዋሪዎች ትምህርት ቤቶቹን  እንደራሳቸው አድርገው ንብረት እንዲጠብቁና እንዲንከባከቡ አሳስበዋል።

የካቺሲ ቀበሌው ነዋሪ  አቶ ነገሮ ቆርሳ የትምህርት ቤቱ መገንባት ልጆቻቸው በአቅራቢያቸው ለመማር እንደሚያስችላቸው ገልጸዋል። በዚህም ተደስቻለሁ ብለዋል፡፡

ቀደም ሲል የአካባቢያቸው ልጆች ትምህርት ፍለጋ ርቀው ይሄዱ እንደነበር ያስታወሱት ነዋሪው፣ትምህርት ቤቱ ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጡ እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።

የእዚሁ ቀበሌ ሌላኛው ነዋሪ አቶ ምስጋና ቁፌ በበኩላቸው ትምህርት ቤቶቹ ልጆቻቸው ራቅ ያለ ቦታ ሄደው በመማራቸው ይባክን የነበረውን ጊዜ፣ ጉልበትና ገንዘብ ከመቆጠብ በተጨማሪ በሴት ተማሪዎች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት እንደሚቀንስ እምነታቸውን ገልጸዋል።

ለትምህርት ቤቱ አስፈላጊውን እንክብካቤና ጥበቃ አደርጋለሁም ብለዋል።