ችሎቱ በአቶ በረከት ስምኦንና አቶ ታደሰ ካሳ ላይ ተጨማሪ የስምንት ቀናት የጊዜ ቀጠሮ ሰጠ

148

ባህርዳር መጋቢት 11/2011  የባህርዳርና አካባቢው ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንደኛ ወንጀል ችሎት በጥረት ኮርፖሬት የቀድሞ ከፍተኛ አመራሮች አቶ በረከት ስምኦንና አቶ ታደሰ ካሳ ክስ ጉዳይ ላልተጠናቀቁ የምርመራ ስራዎች ተጨማሪ የስምንት ቀናት  የጊዜ ቀጠሮ ሰጠ፡፡

በጠበቆቻቸውና በቤተሰቦቻቸው እየደረሰ ያለውን ጫና የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ተከታትሎ እርምጃ እንዲወስድ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡

ችሎቱ መጋቢት 02/2011ዓ.ም. ባስቻለው ችሎት ከዳሽን ቢራ አክሲዮን ማህበር ሽያጭ ጋር በተያያዘ ያላለቁ መረጃዎችን አሰባስቦ መርማሪ ቡድኑ እንዲያጠናቅቅ የስምንት ቀን ጊዜ መስጠቱ ይታወሳል፡፡

በተሰጠው ጊዜ ውስጥም በርካታ ሰነዶችን ከማሰባሰብ በተጨማሪም የኦዲት ስራው ቅዳሜና እሁድን ጨምሮ በመስራት ለማጠናቀቅ ጥረት ማድረጉን መርማሪ ቡድኑ አስታውቋል፡፡

ሆኖም ከአክሲዮን ሽያጩ ውስብስብ አሰራር ጋር ተያይዞ ሆን ተብሎ ሰነዱ  በፋብሪካው እንዳይቀመጥ በመደረጉ የኦዲት ስራውን አስቸጋሪ እንዳደረጋው ተገልጿል፡፡

ኦዲቱን እያደረገ ያለው የክልሉ ዋና ኦዲት መስሪያ ቤት አሁንም ጉዳዩን ማጠናቀቅ እንዳልቻለና በቀጣይም ተጨማሪ ጊዜ እንደሚያስፈልገው በድብዳቤ ማስታውቁን ቡድኑ አመልክቷል፡፡

የሚያስፈልገው ሰነድና እስከ መቼ እንደሚያጠናቅቅ  የጊዜ ሰሌዳውን በዝርዝር በማቅረብ የኦዲት ቡድኑ ማስታወቁ  ተገልጿል፡፡

ያልተጠናቀቁ የኦዲት ስራዎችን ጨርሶ  ለማቅረብም የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ እንዲሰጠው ችሎቱን ጠይቋል፡፡

ተጠርጣሪው አቶ በረከት ስምኦን በበኩላቸው የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን መርማሪ ቡድን ሆን ብሎ ተደጋጋሚ የጊዜ ቀጠሮ በመስጠት ህገ መንግስታዊ መብታችን እየተጋፋ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እሳቸው እንዳሉት  90 በመቶ ምርመራ አጠናቀናል፣ መረጃ አሰባስበናል፣ ለክስ የሚያበቃ ማስረጃ ተገኝቷል በማለት በክልሉ ባለስልጣናት ጭምር መግለጫ ሲሰጥ ቆይቷል፡፡

"ይሁን እንጂ አሁንም ኦዲት አልተጠናቀቀም የሚቀረን ስራ አለ በማለት አላስፈላጊ የጊዜ ቀጠሮ እየጠየቀ ፍርድ ቤቱም በመፍቀድ  መብታችን ሊጠበቅ አልቻለም" ብለዋል፡፡

ለዛሬ የተሰጠው የጊዜ ቀጠሮም ምርመራውን አጠናቆ ለክስ መመስረቻ የሚሆን ጊዜ ለመጠየቅ ቢሆንም አሁንም አልጨረስኩም በማለት እያጉላላቸው መሆኑን አመልክተዋል፡፡

መጋቢት 2 እና 3/2011 ዓ.ም. በዋለው ችሎት ህጋዊ መብታቸውን ተጠቅመው ጠበቃ ቢያቀርቡም እንግልት እየደረሰባቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

" የአማራ ክልል ህዝብ ታላቅ ነው፣ ህግ አዋቂና የተከበረ ኩሩ ህዝብ ነው፤ ነገር ግን ይህን እያደረጉ ያሉት ሆን ተብሎ የተሰማሩ ጉልበተኞች ናቸው " ብለዋል፡፡ 

በመደበኛ ችሎት ጭምር ሲወጡና ሲገቡ  ክብረ ነክ ስድብ እየደረሰባቸው በመሆኑ ችሎቱ ህገ መንግስታዊ መብታቸውን እንዲያስጠብቅላቸው ጠይቀዋል፡፡

አቶ ታደሰ ካሳ  በበኩላቸው" ምርመራውም ሆነ ኦዲቱ መቼ ነው ሊያልቅ የሚችለው ይህ የመርማሪውንም ሆነ የኦዲተሩን የአቅም ውስንነት የሚያሳይ ነው "ብለዋል፡፡

" እኛን የከሰሰን የክልሉ ከፍተኛ አመራር በመሆኑ ምርመራው ሆን ተብሎ በማጓተት እስርቤት እንድንቆይ አላማ ተደርጎ እየተሰራ ነው " ሲሉ አመልክተዋል፡፡

የምርመራ ቡድኑ በተሰጠው ጊዜ ምርመራውን የማያጠናቅቅ ከሆነ ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ ሳይሰጠው በነፃ እንዲለቀቁ ጠይቀዋል፡፡

የምርመራ ቡድኑ በበኩሉ ከ90 በመቶ በላይ ምርመራው ተጠናቋል ተብሎ የተገለፀው ትክክል እንደሆነ ገልጾ በሂደት ላይ ያለው እንዳለ ሆኖ በአቶ ታደሰ ካሳ ላይ ስምንት ተጨማሪ ክስ የተመሰረተባቸው መሆኑን አስታውቋል፡፡

የሁለቱን ክርክር ያዳመጠው ችሎቱ በበኩሉ ተደጋጋሚ ቀጠሮ የሚሰጠው ትክክለኛ ፍትህ ለመስጠትና ጉዳዩን በሚገባ ለማጣራት ያመች ዘንድ እንደሆነ ገልጿል፡፡

የምርመራ ቡድኑ  የዋና ኦዲተር ማስረጃን አክሎ ባቀረበው መሰረትም የዳሽን አክሲዮን የሽያጭ ጉዳይ ለማጣራት ተጨማሪ ጊዜ እንደሚያስፈልገው በማመን የስምንት ቀናት  ተጨማሪ ጊዜ ፈቅዷል፡፡

በዚህም መሰረት መጋቢት 20/2011ዓ.ም.  ከሰዓት በኋላ የኦዲት ስራው ተጠናቆ እንዲቀርብ ችሎቱ አዟል፡፡

በተጨማሪም በጠበቃዎች ላይ ጫና ደርሷል ለተባለው ቅሬታም ማንኛውም ሰው አቅም ካለው ጠበቃ ቀጥሮ ከሌለው ደግሞ መንግስት ቀጥሮለት  እንዲከራከር ህገ መንግስቱ እንደሚፈቅድ ተመልክቷል፡፡

በቤተሰቦቼ ላይ ጫና ተፈጥሯል ስንወጣ ስንገባ እየተሰደብን ነው ተብሎ ለቀረበውም አግባብ እንዳልሆነና ይህን ጉዳይ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ተከታትሎ እርምጃና ማስተካከያ እንዲወስድ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም