ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት አቡዳቢ ገቡ

476

አዲስ አበባ መጋቢት 11/2011 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት አቡዳቢ ገቡ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአቡዳቢ አል-ባቴን አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የአቡዳቢው አልጋወራሽና  የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ምክትል ጠቅላይ የጦር ኮማንደር ሸክ ማህመድ ቢን ዛይድ አቀባበል አድርገውላቸዋል።

በዛሬ ውሏቸውም በአቡዳቢ ብሄራዊ  የኢግዚብሽን ማዕከል በዓለም አቀፍ ልዩ የኦሎምፒክ ጨዋታዎች የሚሳተፉ አትሌቶችን ጎብኝተዋል።

ኢትዮጵያና ኤርትራ ችግሮቻቸውን በሰላማዊ መንገድ መፍታታቸውን ተከትሎ የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ባሳለፍነው ሐምሌ ወር ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይና ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ  የአገሪቱን ከፍተኛ ኒሻን መሸለሟ ይታወሳል።

ኢትዮጵያና ኤርትራ ለሚያደረጉት ሁለንተናዊ ትብብር የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ከጎናቸው እንደምትቆምም በወቅቱ አስታውቃለች። 

በመካከለኛው ምስራቅ ጉብኝት እያደረጉ የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ትናንት ወደ ኳታር አቅንተው ከአሚር ሸክ ተማም ቢን አህመድ ጋር መወያየታቸው ይታወቃል።