ሚኒስቴሩ ከተፈቀደለት የበጀት ርዕስ ውጭ ከ330 ሚሊዮን ብር በላይ ተጠቅሟል – የፌዴራል ዋና ኦዲተር

511

አዲስ አበባ መጋቢት 11/2011 የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በ2009 ዓ.ም  331 ሚሊዮን ብር  የሚጠጋ ገንዘብ ከተፈቀደለት የበጀት ርዕስ ውጭ መጠቀሙን የፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ገለፀ።

ሚኒስቴሩ የተጠቀሰውን ገንዘብ ከመጠቀሙ በፊት የገንዘብ ሚኒስቴርን ፈቃድ ማግኘት እንደነበረበትም ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤቱ አመለክቷል።   

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደር ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚኒስቴሩን የ2009 በጀት ዓመት የሂሳብ ኦዲት ግኝትን ገምግሟል።

የፌደራል ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ እንደገለጹት፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በተጠቀሰው በጀት ዓመት 331 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ከተፈቀደለት በጀት ርዕስ ውጭ የገንዘብ ሚኒስቴርን ፍቃድ ሳያገኝ በጀት አዛውሮ መጠቀሙ በኦዲት ተረጋግጧል።

ሚኒስቴሩ የተጠቀሰውን ገንዘብ ከመጠቀሙ በፊት የገንዘብ ሚኒስቴርን ፈቃድ ማግኘት ነበረበት ያሉት ዋና ኦዲተሩ  “ይህን ባለማድረጉ መንግሥት ያጸደቀውን የፋይናንስ አስተዳደር አዋጅ ጥሷል ፤ ይህም በህግ የሚያስቀጣ ተግባር ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

ከዚህም ሌላ ሚኒስቴሩ በተጠቀሰው በጀት ዓመት ሥራ ላይ እንዲያውለው ከተመደበለት አጠቃላይ በጀት ውስጥ 445 ሚሊዮን ብር አለመጠቀሙን የኦዲት ግኝቱ እንደሚያሳይ ገልጸዋል።

ለሰንዓ ፎረም ተብሎ ከ27 ሚሊዮን ብር በላይ በሚመለከታቸው የሚኒስቴሩ የሥራ ኃላፊዎች ጸድቆ የወጣ ሲሆን ከዚህ ውስጥ የኢትዮጵያ ድርሻ ምን ያህል እንደሆነ የሚገልጽ ማስረጃ ሳይቀርብ ክፍያ መፈጸሙን በኦዲት ምርመራ እንደተደረሰበት አቶ ገመቹ አስረድተዋል። 

ሚኒስቴሩ በካንቤራ፣ በብራስልስና በዋሽንግተን ውል ሳይታሰር እንዲሁም ከመንግስት የግዢ አዋጅ ውጭ ያለ ውድድር ከአንድ አቅራቢ የአምስ ሚሊዮን 953 ሺህ ብር የተለያዩ ግዢዎች መፈጸማቸውን ምርመራው አረጋግጧል።

እንዲሁም የፌደራል መንግስት የግዢ ስርዓትን በጣሰ መልኩ አንድ ሚሊዮን 894 ሺህ ብር የተለያዩ የአገልግሎት ግዢዎች መፈጸማቸውንም አብራርተዋል።

በ2009 በጀት ዓመት በአሜሪካና በካናዳ በሚገኙ ግዛቶች የተደረገን ጉዞ ከአንድ አገር ወደ ሌላ አገር የተደረገ ጉዞ በሚል ከመንግስት መመሪያ ውጪ ለመልካም አገልግሎት ክፍያ ለዲፕሎማቶች የተከፈለው ገንዘብ ለመንግስት ተመላሽ መደረግ እንዳለበት ዋና ኦዲተሩ ተናግረዋል። 

አንድ ዲፕሎማት ከአንድ አገር ወደ ሌላ አገር ሲሄድ 50 ዶላር የመልካም አገልግሎት ክፍያ እንዲፈጸም መመሪያው እንደሚፈቅድ ገልጸው ከዚያ ውጭ ግን ከአንድ አገር ግዛት ወደ ሌላ አገር ግዛት ለተደረገ ጉዞ ክፍያ እንደማይፈጸም አቶ ገመቹ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት በአህጉርና ዓለም አቀፍ ተቋማት የአባልነት መዋጮ በሚከፍልበት ወቅት አገሪቱ አባል ከሆነችበት ተቋም የክፍያ ጥያቄ ማረጋጋጫ ደብዳቤ መቅረብ እንዳለበትም ጠቅሰዋል።

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ምክትል ዋና ኦዲተር ወይዘሮ መሠረት ዳምጤ በበኩላቸው ሚኒስቴሩ ማስረጃ ሳያቀርብ ለሚፈፅማቸው  ክፍያዎች በቂ ማስረጃ እንዲያቀርብ ሲጠየቅ እያቀረበ አይደለም ብለዋል።

የአፍሪካ ኀብረትን ጨምሮ ሌሎች አህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ስብስባዎች በኢትዮጵያ እንደሚካሄዱ አስቀድሞ የሚታወቅ መሆኑን የገለጹት ወይዘሮ መሰረት ሚኒስቴሩ ሆቴሎችን አወዳድሮ ከሆቴሎች የስብስባ መስተንግዶና አገልግሎት አሰጣጥ ጋር የተያያዘ የማዕቀፍ ግዢ ስምምነት ማድረግ ላይ ችግር እንዳለበት ተናግረዋል።

ለ3ኛ ወገን የሚደረግ ወጪ በቀጥታ ከተቋማቱ በጀት ተቀንሶ ወደ ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ሂሳብ እንዲተካ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤትና ገንዘብ ሚኒስቴር መመሪያ መስጠቱን ምክትል ዋና ኦዲተሯ አመልክተዋል።

በአጠቃላይ በአሁኑ ወቅት ሚኒስቴሩ የኦዲት ግኝቶቹን መሠረት በማድረግ እርምጃ ለመውሰድ ያሳየው ተነሳሽነት መልካም እንደሚባልና ይሄንንም አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በበኩላቸው ሚኒስቴሩ በኦዲት ግኝቱ ውስጥ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ከሐምሌ ወር 2009 ዓ.ም እስከ ታህሳስ ወር 2010 ዓ.ም የሚቆይ የድርጊት መርሃ ግብር ቀርጾ የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ሚኒስቴሩ አብዛኞቹን ስራዎች የሚያከናውነው በውጭ አገሮች በመሆኑ ስራ የሚስራባቸው አገሮች የፋይናንስ ህጎች ከአገሪቱ ጋር አለመጣጣም እንቅፋት እየሆነበት መሆኑን አስረድተዋል። 

በቀጣይ ችግሮቹን ለማቃለል የመዋቅር ጥናት በማድረግ የኮሚቴዎችን አሰራር የማጠናከር ተግባር እየተከናወነ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

ከሐምሌ ወር 2011 ዓ.ም ከተሰብሳቢ ሂሳቦችና ከሚፈጸሙ ግዢዎች ጋር በተያያዘ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት የፋይናንስ አስተዳደር መመሪያ ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

በቂ ማስረጃ የማይቀርበው ከሰነድ አለመያያዝ ጋር ባለ ችግር ምክንያት በመሆኑ የሰነድ አያያዝ ችግር የማስተካካል እርምጃ እንደሚወሰድም ገልጸዋል። 

በአጠቃላይ የፌደራል ዋና ኦዲተር ያቀረባቸውን ሀሳቦች መሠረት በማድረግ የማስተካከያ እርምጃ ለመውሰድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቁርጠኛ መሆኑን ወይዘሮ ብርቱካን አረጋግጠዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደር ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ መሐመድ የሱፍ በሰጡት ማጠቃለያ  የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተመደበለትን በጀት ለታለመት ዓላማ ከማዋል አንጻር ሰፊ ስራ መስራት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

ሚኒስቴሩ የመንግስት ሀብትና ንብረት በመንግስት አዋጆች መሠረት በአግባቡ መጠቀም እንዳለበት እንዲሁም ከግዢ፣ ከክፍያና ከተሰብሳቢ ሂሳብ አያያዝ ጋር በተያያዘ የቀረቡበትን ችግሮች በአፋጣኝ መፍትሄ መስጠት እንዳለበት ገልጸዋል።

ሚኒስቴሩ የውስጥ ኦዲተር አቅሙን የማጎልበትና የሚመደብለትን በጀት አጠቃቀም ላይ ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል ማድረግ እንዳለበትም አስታውቀዋል።   

በፌደራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት የቀረቡ ክፍተቶችን በማጤን አስቸኳይ የማስተካከያ እርምጃ መወስድ እንዳለበትም የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ  አቶ መሐመድ አሳስበዋል።