የትምባሆ ቁጥጥር ስምምነት የማስፈጸሚያ የህግ ማዕቀፍን ያካተተው ረቂቅ አዋጅ በሰኔ ወር ይጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል

177
አዲስ አበባ ግንቦት 23/2010 የትምባሆ ቁጥጥር ስምምነት የማስፈጸሚያ የህግ ማዕቀፍን ያካተተው ረቂቅ አዋጅ በሰኔ ወር ይጸድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ የኢትዮጵያ ምግብ፣ የመድሃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን አስታወቀ። የዓለም ትምባሆ የማይጨስበት ቀን በዓለም ለ31ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ለ26ኛ ጊዜ ‘ትምባሆና የልብ ህመም’ በሚል መሪ ቃል ዛሬ ተከብሯል። የልብ ህመም በአለም አቀፍ ደረጃ ገዳይ ከሆኑ በሽታዎች በአንደኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን ለትምባሆና ለሲጋራ ጪስ የተጋለጡ ሰዎች 12 በመቶ የሚሆኑት ለሁሉም አይነት የልብ ህመሞችና ሞት የተጋለጡ ናቸው። የኢትዮጵያ ምግብ፣ የመድሃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኬይረዲን ረዲ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ የአለም የጤና ድርጅት ያወጣውን የትምባሆ ቁጥጥር ስምምነት ተቀብላ በ2006 ዓ.ም ብታጸድቅም የማስፈጸሚያ የህግ ማዕቀፍ የማዘጋጀቱ ስራ ጊዜ ወስዷል። የማስፈጸሚያ የህግ ማዕቀፍ ያካተተው ረቂቅ አዋጅ ታይቶ ለሀዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቧል ብለዋል። ህዝብ የተሰበሰባቸው ስፍራዎች ላይ ትንባሆ እንዳይጨስ የተለየ ማጨሻ ቦታ ማዘጋጀት፣ የትምባሆ ፓኬት ቢያንስ 70 በመቶ የሚሆነው የጽሁፍና የስዕል ማስጠንቀቂያ እንዲኖራቸው ማድረግ በረቂቅ አዋጁ ከተካቱት ጉዳዮች ውስጥ ይጠቀሳሉ። ትምባሆ በየትኛውም አማራጭ እንዳይተዋወቅና ሲጋራ ከፓኬት ውጪ በፍሬ እንዳይሸጥና ከ18 አመት በታች ለሆኑ ህጻናት እንደዳይሸጥ መከልከልም ተካተዋል። ባለፉት አመታት ባለስልጣኑ የማጽደቂያ አዋጁን ረቂቅ የህግ ዝግጅት፣ በአገር አቀፍ ደረጃ ሁሉም ሴክተር መስሪያ ቤቶች በትምባሆ ቁጥጥር ላይ እንዲሰሩ የትምባሆ ቁጥጥር ኮሚቴ የማዋቀር ስራዎችን ማከናወኑን ጠቅሰዋል። አገር አቀፍ የትምባሆ ስትራቴጂክ ፕላን የማዘጋጀት፣ ክልሎች የትምባሆ ከልካይ ህግ እንዲያወጡ የማድረግ፣ ሕዝብ በተሰበሰባቸው ስፍራዎች ትምባሆ እንዳይጨስ የማስተማርና የመከለል፣ ህገ ወጥ የትምባሆ ንግድ ቁጥጥር የማጠናከር ስራዎች መሰራታቸውን ተናግረዋል። በትምባሆ ምርት ላይ እንዲጣል የተጠየቀው ከፍተኛ ግብር መዘግየቱ፣ ሕዝብ በተሰበሰባቸው ስፍራዎች ትምባሆ እንዳይጨስ የሚከለክለው ህግ ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ያለመሆን፣ ሁሉም ክልሎች እንደ ተጨባጭ ሁኔታው የህግ ማዕቀፍ ያለማውጣት ከተግዳሮቶች ውስጥ ጠቅሰዋል። መገናኛ ብዙሃን፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትና ሲቪክ ማህበራት ስለ ትምባሆ አስከፊነት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ያለመስራት፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በትምባሆ የጤና ጉዳት ላይ የምርምር ስራዎችን ያለመስራት ክፍተት መኖሩን ጠቁመዋል። የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከባለስልጣኑ ጋር በመተባበር እ.ኤ.አ በ2016 ባካሄደው ጥናት ከ15 ዓመት በላይ የሆናቸው ዜጎች በአገሪቱ የትምባሆ ተጠቃሚዎች ቁጥር ከ3 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ መሆኑን ያመላክታል። 6 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚሆኑ እንደ ሆቴል፣ መዝናኛ ቤቶች፣ ዩኒቨርሲቲዎችና መሰል ቦታዎች የሚሰሩ ኢትዮጵያውያን ለሁለተኛ ወገን አጫሽነት ተጋልጠዋል። የአለም የጤና ድርጅት እ.ኤ.አ በ2018 ባወጣው ሪፖርት ላይ እንዳመለከተው በአለም በትምባሆ ምክንያት በየዓመቱ ከ7 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች ህይወት ያልፋል። ከነዚህ ውስጥ ከ 890 ሺህ በላይ የሚሆኑት ሰዎች ትምባሆን በቀጥታ የማይጠቀሙ የሁለተኛ ወገን አጫሽነት ምክንያት ህይወታቸው እንደሚያልፍ ሪፖርቱ ጨምሮ ገልጿል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም