የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዘመናዊ የክፍያ ስርዓት ለመዘርጋት እየሰራ ነው

104

አዲስ አበባ መጋቢት 11/2011 የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የዘመናዊ ክፍያ ስርዓት ተግባራዊ ለማድረግ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች በማከናወን ላይ መሆኑን አስታወቀ።

ደንበኞች የኤሌክትሪክ ፍጆታ ሂሳባቸውን በዘመናዊ መንገድ ክፍያ መፈጸም እንዲችሉ ተግባራዊ የሚደረገው አሰራር ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በመተባበር ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት የደንበኞችን መሰረታዊ መረጃዎች የማሰባሰብ ስራ እየተከናወነ ሲሆን አሰራሩ ተግባራዊ የሚደረገው ከደንበኞች የሚፈለጉ መረጃዎች ከተሰበሰቡና የውል ስምምነት ከተፈጸመ በኋላ ነው፡፡

ዘመናዊ የክፍያ ስርዓቱ ተጠቃሚ የሚሆኑት የንባብ ቆጣሪ የሚጠቀሙ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚዎች ናቸው።

ፍቃደኛ የሆኑ ዝቅተኛ የኃይል ተጠቃሚ ደንበኞችም በክፍያ ስርዓቱ ተጠቃሚ መሆን እንደሚችሉም ገልጿል።

የክፍያ ስርዓቱ ደንበኞች የተጠቀሙበትን የኤሌትሪክ አገልግሎት ክፍያ በዘመናዊ አሰራር ለመሰብሰብ የሚያስችል ከመሆኑም በላይ ለደንበኞች ቀልጣፋና ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት የሚያግዝ ነው።

እንዲሁም የደንበኞች መረጃ በባንኩና በተቋሙ ዘንድ በጥንቃቄ የሚያዝ በመሆኑ ከዚህ በፊት ወርሃዊ ፍጆታን ለመክፈል የሚባክነውን ጊዜ የሚያስቀር እንደሆነም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታውቋል። 

''ደንበኞች ወርሃዊ የክፍያ ጊዜን ከመዘንጋት ጋር በተያያዘ የሚከሰተውን ተጨማሪ የጊዜና የገንዘብ ብክነት የሚታደግ ነው'' ብሏል።

ደንበኞች ከባንክ ተቀማጭ ሒሳባቸው ተቀናሽ የተደረገውን የገንዘብ መጠን የሚገልጽ የገቢ ደረሰኝ ከተቋሙ የሚዘጋጅላቸው ሲሆን ደንበኞች ከተቀማጭ ሒሳባቸው ተቀናሽ ስለተደረገው ገንዘብ መረጃ አጭር የጽሑፍ መልዕክት በተንቀሳቃሽ ስልካቸው ይደርሳቸዋል።

ከፍተኛ ኃይል የሚጠቀሙ ደንበኞችና ፍቃደኛ የሆኑ ዝቅተኛ የኃይል ተጠቃሚዎች በአቅራቢያቸው በሚገኝ የኢትዮጵያ ኤሌትሪክ አገልግሎት መስጫ ማዕከላት ስምምነታቸውን በተዘጋጀው ቅጽ ላይ እንዲያሳውቁ ጥሪ ተደርጓል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከፍተኛ ኃይል ተጠቃሚ ደንበኞች የኤሌክትሪክ ፍጆታ ሂሳባቸውን በባንክ በኩል ክፍያ እንዲፈጽሙ  የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ጥር 13 ቀን 2011 ዓ.ም መፈራረሙ ይታወሳል፡፡   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም