በሐረሪ ህግን የማስከበር ሥራ በተቀናጀ መልኩ መጀመሩን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ

51

ሀረር መጋቢት 11/2011 ህገ ወጥ ድርጊቶችን የመከላከልና ህግን የማስከበር ሥራ በተቀናጀ መልኩ የመስራት ሥራ መጀመሩን የሐረሪ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

በከተማው የሚገኙ አንዳንድ ነዋሪዎች በበኩላቸው በክልሉ ህግን ለማስከበር የተጀመረው ሥራ በተጠናከረ መልኩ መቀጠል እንዳለበት ለኢዜአ ተናግረዋል።

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ረነዳን ኡመር  እንዳሉት በክልሉ ባለፉት ወራት የህግ የበላይነትን የሚፈታተኑ የወንጀል ድርጊቶች ሲከናወኑ ቆይተዋል። 

ይህንን ለመከላከል የጸጥታ ኃይሉ የአቅሙን እየሰራ ቢሆንም የህዝቡን ፍላጎት ማሟላት ባለመቻሉ ቅሬታ ሲፈጥር መቆየቱን አስታውሰዋል።

በተለይ ህገወጥ የጎዳና ላይ ንግድ፣ ያለ መንጃ ፈቃድና ታርጋ ሳይለጥፉ ማሽከርከር፣ ዝርፊያ፣ ህገ ወጥ የመሬት ወረራና ሌሎች ህገ ወጥ ተግባራት በስፋት ሲፈጸሙ እንደነበር ገልጸዋል።

ኮሚሽነር ረነዳን እንዳሉት በአሁን ወቅት ከፌዴራል ፖሊስ፣ ከመከላከያ ሰራዊት፣ ከማረሚያ ፖሊስ ኮሚሽን አባላትና ከደንብ ማስከበር ሠራተኞች ጋር  በቅንጅት ህግን የማስከበር ሥራ እየተከናወነ ይገኛል።

በከተማው ህግን የማስከበር ሥራ መጀመሩ ተከትሎ በተለይ መናኽርያ እና ሲጋራ ተራ ተብለው በሚጠሩ የከተማው አካባቢዎች የሚስተዋሉ ህግ ወጥ የጎዳና ንግድ፣ የትራፊክ እንቅስቃሴና ሌሎች ህገ ወጥ ተግባራት መቀነሳቸውን አስታውቀዋል።

ህብረተሰቡና  የደንብ አስከባሪ ሠራተኞችና ከፖሊስ አባላት ጋር ህግን በማስከበር ሂደት በንቃት እየተሳተፉ መሆኑን ጠቁመው በቀጣይም ይህ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።

የሐረሪ ክልል ደንብ ማስከበር ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር አብዲ ሳኒ በበኩላቸው እንዳሉት በአገሪቱና በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች ተከስቶ በነበረ አለመረጋጋት ጋር ተያይዞ በከተማው ህግ ወጥ የመንገድ ዳር ንግድና የቤንዚል ግብይት ተስፋፍቶ ቆይቷል።

"ይህም በተለይ በህጋዊ እና ግብር ከፋይ ነጋዴው ላይ  ቅሬታን ማሳደሩንና  የመንገድ መጨናነቅ በማስከተል በትራፊክ ፍሰቱ ላይ ተጽዕኖ ሲፈጥር ቆይቷል" ብለዋል።

ጽህፈት ቤቱ ህገወጥነትን ለመከላከል ከክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በመተባበር ባደረገው እንቅስቃሴ 2ሺህ 200 ሊትር በጎዳና ላይ ሲሸጥ የነበረ ቤንዚል በቁጥጥር ስር ማዋሉን ገልጸዋል።

በአጭር ጊዜ በተደረገ ጥረት 90 በመቶ የሚሆን የጎዳና ንግድ እንቅስቃሴ መቆሙን የጠቆሙት ኃላፊው "በቀጣይም ይህን ጨምኖ ህግ ወጥ ግንባታን፣ ግብር አለመክፈልና በሌሎች ህግን ያልተከተሉ ስራዎች ላይ ህግን የማስከበር ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል" ብለዋል።

በከተማው መናኽርያ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ የትራንስፖርት ስምሪት ሥራ የሚያከናውኑት አቶ ተረፈ መስፍን በበኩላቸው ህግን ያልተከተሉ ሥራዎች በስፍራው ሲከናወኑ እንደነበረና ለስራቸው አስቸጋሪ ሁኔታ ፈጥረው እንደነበር አስታውሰዋል።

በአሁኑ ወቅት የጸጥታ ኃይሉ በቅንጅት የጀመረው ሥራ ውጤት እያሳየ መሆኑንና ይህም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አመልክተዋል።

በከተማው የነበረው ህገ ወጥ የጎዳና ላይ ንግድ በህጋዊ ነጋዴው ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሷድሮ ቆይቷል፤ ለመንግስትም ማስገባት የሚገባንን ግብር በአግባቡ ለመክፈል እንቅፋት ፈጥሮብን ቆይቶ ነበር" ያሉት ደግሞ በሐረር ከተማ በኤሌክትሮኒክስ ንግድ ሥራ የተሰማሩት አቶ በለጠ ይገረም ናቸው።

" በከተማው ህግን የማስከበር ሥራ በመጀመሩ ገቢያችን እየተሻሻለ ይገኛል፤ በመሆኑም በክልሉ የተጀመረው ህግን የማስከበር ሥራ  በተጠናከረ መልኩ መቀጠል ይኖርበታል" ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት የኢዜአ ሪፖርተር በከተማው ተዘዋውሮ እንደተመለከተው ከዚህ ቀደም የነበረው ህገ ወጥ የጎዳና ንግድና በከተማው መናኽርያ አካባቢ ይፈጸሙ የነበሩ የወንጀልና ህገ ወጥ ስራዎች  እየቀነሱ መምጣታቸውን ታዝቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም