በምዕራብ ጎንደር ዞን ነዋሪው ሰላማዊ ሕይወት መኖር ጀምሯል - የዞኑ አስተዳደር

102

ጎንደር መጋቢት 11/2011 በምዕራብ ጎንደር ዞን በተሰራው ጠንካራ የማረጋጋት ሥራ የአካባቢው ሰላም ሙሉ በሙሉ መመለሱንና ነዋሪውም ሰላማዊ ሕይወት መኖር እንደጀመረ የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ፡፡

በቅማንትና በአማራ ህዝቦች መካከል ተከስቶ የነበረውን አለመግባባት ለመፍታትና የአካባቢውን ሰላም ዘላቂ በሆነ መልኩ ለመጠበቅ የሁለቱን ህዝቦች ተወካይና የሃይማኖት አባቶች በማገናኘት የማቀራረብ ሥራ እየተሰራ መሆኑን የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አደባባይ ሙሉጌታ ተናግረዋል፡፡

አካባቢውን ለማረጋጋት በተሰራው ስራም በቡድንም ሆነ በግል በመንቀሳቀስ ሲፈጸም የነበረ ሰው የማገትና የመግደል ተግባር፣ ንብረት የማውደምና፣ መፈናቀል፣ መኪና አስቁሞ መዝረፍና የመሳሰሉት ተግባራት በአሁኑ ወቅት መቆማቸውን ገልጸዋል፡፡

ከሁለቱም ብሔረሰብ ህዝቦች የተውጣጡ 246 ሰዎች በተገኙበት የሰላምና የእርቅ መድረክ መጋቢት 6 ቀን 2011 ዓ.ም መደረጉን አስታውሰው በመጪው እሁድም ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት የሁለቱ ህዝቦች መድረክ እንደሚካሄድ አመልክተዋል።

በነበረው አለመረጋጋት ከአካባቢያቸው የተፈናቀሉ ሰዎችን ወደ ቀያቸው ለመመለስና ለማቋቋም ገቢ አሰባሳቢ ኮሚቴ ከዞን ጀምሮ እስከ ቀበሌ ድረስ እንዲዋቀር ተደርጓል ብለዋል፡፡

በግጭቱ ቀጥተኛ ተሳትፎ አላቸው ተብለው የተጠረጠሩ 47 ሰዎች በጥምር የፀጥታ ኃይሉ ተይዘው በህግ ጥላ ስር እንደሚገኙም ጠቁመዋል፡፡

ከሀገር ሽማግሌዎች መካከል የገንዳውሃ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ጓዴ አራጋው የአካባቢውን ሰላም ለመመለስ መንግስት እየወሰደ ያለውን እርምጃ እንደሚደግፉ ገልጸዋል።

" በወንድማማች ህዝቦች መካከል የተፈጠረውን የጥል ገመድ እንበጥሰዋለን " ያሉት አቶ ጓዴ ንብረት ለወደመባቸው ግለሰቦች መላ ህዝቡ ድጋፍ እንዲያደርግ በማስተባበር ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል፡፡

"አሁን የተፈጠረው ሰላም ዘላቂ እንዲሆን ሁለቱን ህዝቦች ማቀራረብና የተበደለን መካስ ይገባል" ያሉት ደግሞ ከመተማ ወረዳ መቃ ቀበሌ የመጡት አቶ አስቻለው ጋሸ ናቸው ፡፡

መንግስት የሚያደርገውን ድጋፍ ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ማከፋፈል እንዳለበት ጠቁመው፣ እርቁ የሰመረና የነበረ ፍቅርን ሚያጠናክር ሆኖ እንዲቀጥል የራሳቸውን ድርሻ እንደሚወጡ ገልፀዋል፡፡

ሌላው የገንዳ ውሃ ከተማ ነዋሪ ወጣት አምሳሉ ተገኝ በበኩሉ አሸናፊና ተሸናፊ በሌለው ግጭት ከሁለቱም ወገን የሰው ሕይወት መጥፋቱና ንብረት መውደሙ እንዳሳዘነው ተናግሯል፡፡

" አባትና ልጅ፣ ወንድምና ወንድምን መለያየት እጅግ ይከብዳል" ያለው ወጣቱ፣ ከሁለቱም ህዝቦች ያሉ ወጣቶችን በማገናኘት የነበረ ፍቅራቸውን ማደስ እንደሚገባ ተናግሯል፡፡

በምዕራብ ጎንደር ዞን  ሁሉም ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች ተከስቶ በነበረ አለመረጋጋት ከመተማ ወደ ጎንደርና ባህር ዳር ከተሞች የሚወስደው መንገድ ለአራት ወራት ያህል ተዘግቶ መቆየቱንና ከየካቲት ወር 2011 ዓ.ም ጀምሮ ክፍት መሆኑ ይታወሳል።

በዞኑ ተከስቶ በነበረው አለመረጋጋት ከአምስት ሺህ በላይ የሕብረተሰብ ክፍሎች ከቤት ንብረታቸው እንደተፈናቀሉ የዞኑን አስተዳደር ጽህፈት ቤትን አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም