በሶማሌ ክልል ተሿሚዎች የሀብት ምዝገባ እንዲያካሂዱ ረቂቅ አዋጅ እየተዘጋጀ ነው

72

ጅግጅጋ መጋቢት 11/2011 በሶማሌ ክልላዊ መንግስት ተሿሚዎች የሀብት ምዝገባ እንዲያካሄዱ የሚያስገድድ ረቂቅ አዋጅ መዘጋጅቱን የክልሉ ስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ።

በክልሉ በየደረጃው ያሉ አመራሮች ሀብታቸውን በማስመዝገብ የህዝብ ሀብት ማዳን በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ግንዛቤ ለመፍጠር የሚያስችል የአቅም ግንባታ ስልጠና በጅግጅጋ ከተማ ለባለሙያዎች እየተሰጠ ነው።

የፌዴራል ስነ ምግባርና ፀረ ሙሴና ኮሚሽን ባዘጋጀው ስልጠና ላይ የተገኙት የክልሉ ስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አብዲ ሐሰን እንዳሉት በክልሉ ተጠያቂነት ያለው አሰራረን ለማስፍን በትኩረት እየተሰራ ነው።

ሙስናና ያልተገባ ጥቅምን ለመከላከል በሚደረጉ ጥረቶች በክልሉ ተሿሚዎች ያላቸውን ሀብት እንዲያስመዘግቡ የሚያስገድድ ረቂቅ አዋጅ በክልሉ የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

"በአሁኑ ወቅትም ረቂቅ አዋጁን ለክልሉ ምክር ቤቱ ጉባኤ ለማቅረብ እየተሰራ ነው" ብለዋል።

ኮሚሽነር አብዲ እንዳሉት የሀብት ማስመዝገብ ሥራው በክልሉ ተጠያቂነትን ለማስፋን ኮሚሽኑ ለሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች አጋዥ ነው።

በአዋጁ መሰረት በክልሉ የሀብት ምዝግባ የሚያደርጉት ተሿሚዎችና አማካሪዎች፣ በመንግስት መስሪያ ቤቶችና በመንግስት የልማት ድርጅቶች በከፍተኛ አመራርነት የሚሰሩ ናቸው።

በተጨማሪም የሀብት ምዝገባው በመምሪያ ኃላፊነት፣ በዳይሬክተርነት፣ በአገልግሎት ኃላፊነትና በተመጣጣኝ የሥራ ደረጃ ላይ  ያሉ ሠራተኞችን እንደሚመለከት አስታውቀዋል።

"ፍቃድ የመስጠት፣ የመቆጣጠር ወይም ግብር የመሰብሰብ ሥራ የሚያከናወኑ የመንግስት ሠራተኞች፣ ዐቃቤ ሕጎች፣ መርማሪዎችና የትራፊክ ፖሊሶችም  በምዝገባው ይካተታሉ" ብለዋል ኮሚሽነር አብዲ።

የፌዴራል ስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አየልኝ ሙሉ በሀገሪቱ አደጋ የሆነውን ሙስናን ለመከላከል በጋራ መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል።

ኮሚሽኑ በመላ ሀገሪቱ ሀብት የማስመዝገብ ሥራን ተግባራዊ ባላደረጉ ሶማሌ፣ አፋርና ጋንቤላ ክልሎች ተግባራዊ እንዲሆን ኮሚሽኑ እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም ገልጸዋል።

ለእዚህም ኮሚሽኑ ከዓለም አቀፍ ተባባሪ ድርጅቶች ጋር በመተባበር በአቅም ግንባታ ስልጠና ድጋፍ የመስጠት ሥራ መጀመሩን ልጸዋል።

የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ተቋም ሙስናን የሚፀየፍ ስነ ምግባር ያለው ትውልድ ለመገንባት የሕብረተሰቡን ግንዛቤ የማሳደግ ሥራ መስራት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

ለአራት ቀናት ለባለሙያዎች እየተሰጠ ያለው የአቅም ግንባታ ስልጠና ሙስናን መከላከል በሚያስችሉ ጉዳዮችና ሀብት ማስመዝገብ ባለው ጠቀሜታዎች ላይ ያተኮረ መሆኑ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም